ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያለ አግልግሎት የቆየው ሰንበቴ ባቡር ጣቢያ ጉዳት ደረሰበት
ተገንብቶ ተጠናቋል የተባለለት የአዋሽ-ኮምቦልቻ ባቡር መንገድ እስካሁን አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩ የሚታወስ ነው
ጣቢያው ጉዳት የደረሰበት ከሰሞኑ በአካባቢው ካጋጠመው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል
የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ወልዲያ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር የግንባታ ፕሮጄክት አካል በመሆን በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የተገነባው የሰንበቴ ባቡር ጣቢያ ጉዳት ደረሰበት፡፡
ባቡር ጣቢያው “ለጅሌ ጥሙጋ እና ለአጎራባቹ ኤፍራታና ግድም ወረዳ ማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ ከሰንበቴ ከተማ በ6 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ” መገንባቱን ያስታወቀው የወረዳው ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጉዳት እንደደረሰበት በማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡
ኮሙኒኬሽን ቢሮው በጣቢያው የነበሩ ኮምፒውተሮች፣ ቴሌቪዥኖች፣ የልብስ ማጠቢያ እና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች መዘረፋቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡
ጣቢያው ደረሰበት ስለተባለው ጉዳት አል ዐይን አማርኛ የጠየቃቸው የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ወልዲያ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር የግንባታ ፕሮጄክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም አማንም ጉዳቱን አረጋግጠዋል፡፡
“ከሰሞኑ በአካባቢው ካጋጠመው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ” መጎዳቱንም ነው የገለጹት፡፡
“ወደ ስፍራው መግባት የተቻለው ዛሬ ነበር” ያሉት ኢንጂነር አብዱልከሪም የደረሰውን ዝርዝር ጉዳት ነገ ለይተን እናሳውቃለን ብለዋል፡፡
ጣቢያው በማን ጉዳት ሊደርስበት እንደቻለ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ ኃላፊነቱን የወሰደ አለበለዚያም እከሌ ነው በሚል ያሳወቀ አካልም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልነበረም፡፡
ጣቢያው ተገንብቶ ከተጠናቀቀ ከሁለት የሚልቁ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ያለ አንዳች አገልግሎት ነው ተቀምጦ ያለው፡፡
ከውጭ በተገኘ ብድር ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ ተደርጎበት በዘመናዊ መንገድ የተገነባው ጣቢያ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ጉዳት ደርሶበት በማየታቸው እጅግ ማዘናቸውንም ነው ስራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
የፕሮጄክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማለትም እስከ ኮምቦልቻ ያለው 270 ኪሎ ሜትር ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡ ሆኖም እስካሁን የጀመረው ምንም ዓይነት አገልግሎት የለም፡፡
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች የሰንበቴ፣ የአጣዬ፣ የሸዋሮቢት፣ የማጀቴ እና ሌሎችም ኪስ አካባቢዎች ያጋጠመው ሰሞነኛ የጸጥታ ችግር ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ለሞት፣ ለስደት እና ለከፍተኛ የንብረት ውድመት እንደዳረገ ይነገራል፡፡
አሁንም አልፎ አልፎ የሚሰሙ የተኩስ እሩምታዎች እንዳሉበት በሚነገርለት በዚህ ግጭት በርካቶች መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷል፡፡
የፌዴራል የጸጥታ አካላት ጭምር ገብተው ሁኔታውን እንዲያረጋጉ ያስገደደ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡