የአዋሽ-ኮምቦልቻ ባቡር መስመር እስካሁን ስራ ያልጀመረው በሁለት ባንኮች አለመግባባት ምክንያት ነው ተባለ
99 በመቶ ያህል የተጠናቀቀው የግንባታ ፕሮጄክቱ በኃይል እጦት ምክንያት ያለፉትን 2 ዓመታት ያለ አገልግሎት መቆየቱ የሚታወስ ነው
በባንኮቹ መካከል ያለው ችግር ከተፈታ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ስራ ሊገባ ይችላል ተብሏል
በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያልቻለው የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ወልደያ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጄክት ሌላ ችግር ገጥሞታል።
ፕሮጄክቱ በአብዛኛው መጠናቀቁ ቢነገርም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት እስካሁን አገልግሎት መስጠት አልጀመረም፡፡
99 በመቶ ያህል ተገንብቶ መጠናቀቁ የሚነገርለት እና ከአዋሽ ኮምቦልቻ የተዘረጋው የግንባታ ፕሮጄክቱ ምዕራፍ የኃይል ማከፋፈያ እና ማስተላለፊያ ጣቢያዎች ተገንብተውለት እንኳን እስካሁን ስራ አልጀመረም፡፡
ለዚህ ምክንያቱ የኃይል አቅርቦት ከግምት ውስጥ አለመግባቱ ነው በሚል ይነገራል፡፡
አል ዐይን አማርኛም የፕሮጄክቱ ከፊል ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ተጠናቆ ሳለ የኃይል አቅርቦት ለምን ምክንያት ሊሆን ቻለ ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልን ጠይቋል።
የተቋሙ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን “ለፕሮጀክቶቹ መጓተት እኛ ሃላፊነት አንወስድም” ብለዋል።
አቶ ሞገስ የግንባታ ፕሮጄክቱ ሲጀመር ኃይል ከግምት ውስጥ አለመግባቱን ነው ይገልጻሉ፡፡
“የግንባታ ፕሮጄክቱ ባለቤት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ባቡር እየገነባ የግድ ኃይል እንደሚያስፈልግ የገባው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ነው” ሲሉም ነው ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ የሚያስቀምጡት፡፡ ይህ “ትልቁ ችግር ነበር”ም ብለዋል።
ሆኖም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እና አመራሮች ባደረጉት ውይይት ለዚህ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ለማስገባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመመደብ ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።
መንግስት ለዚህ ፕሮጀክት ሁለት አበይት ስራዎችን ለመስራት የሃይል ማስተላለፊያ መስመር በ11 ሚሊዮን ዶላር እና 133 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለሀይል ማሰራጫ ጣቢያ (ሰብ ስቴሽን) ግንባታ 5.3 ሚሊዮን ዶላር እና 41 ሚሊዮን ብር መመደቡን አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
የሃይል ማሰራጫ እና መከፋፋያዎችን ለመገንባት ሁለት የቻይና ተቋራጮች ባሳለፍነው ሰኔ 2012 ዓ.ም የግንባታ ስምምነት ከመንግስት ጋር ፈጽመው ነበር።
የግንባታ ስምምነት ውሉ ከ8 ወር በፊት የተፈጸመ ነው፡፡ ሆኖም እስካሁን የተገነባ ነገር የለም፡፡ ይህ ለምን ሊሆንና ግንባታው በምን ምክንያት ሊዘገይ እንደቻለ አል ዐይን የጠየቃቸው አቶ ሞገስ ችግሩ ከውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ጋር እንደሚያያዝ ገልጸዋል፡፡
መንግስት በጀቱን በንግድ ባንክ በኩል ቢለቅም ተቋራጮቹ ዋስትናቸውን ከአዋሽ ባንክ በማምጣታቸው በሁለቱ ባንኮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ስራው ዘግይቷል ብለዋል አቶ ሞገስ።
ከዋስትና ጋር በተያያዘ በሁለቱ ባንኮች መካከል ያለው ችግር ከተፈታ የዲዛይን ስራዎችን እና ሌሎች ቀሪ ስራዎችን በአንድ ወር ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ሊገቡ እንደሚችሉም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
የግንባታ ፕሮጄክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም አማን በበኩላቸው “የመጀመሪያው ምዕራፍ የባቡር መሰረተ ልማት ስራዎች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ብቻ በመጠባበቅ ላይ ነን” ብለዋል።
የባቡር መስመሩ “በኤሌክትሪክ እንደሚሰራ ይታወቃል፤ ስራው ሲጀመር ጀምሮም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተነጋግረንና ተስማምተን ነው ወደ ስራ የገባነው” የሚሉት ስራ አስኪያጁ የዲዛይን ችግር እንደሌለበትም ነው የሚናገሩት፡፡ ይሄንን “የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል”ም ያውቃል ብለዋል፡፡
ግንባታው ከ2 ዓመታት በፊት ቢጠናቀቅም በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት እስካሁን ሙከራ ለማድረግ አለመቻሉንም ገልጸዋል።
“የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ባለመዘርጋቱ ምክንያት ፕሮጀክቱን የገነባው ስራ ተቋራጭ ክፍያ እንዲከፈለው ጠይቋል” ያሉት ስራ አስኪያጁ የኢትዮጵያ መንግስት “ለኩባንያው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ” መሆኑንም ተናግረዋል።
392 ኪሎ ሜትሮችን የሚረዝመው የአዋሽ - ኮምቦልቻ- ወልደያ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር የግንባታ ፕሮጀክት ከ5 ዓመታት በፊት ነው በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የተጀመረው፡፡
ፕሮጄክቱ በሁለት የግንባታ ምዕራፍ ተከፍሎ የሚገነባ ሲሆን የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ ያለውን 270 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው፡፡
ይህ የመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍ 99 በመቶ ተጠናቋል፡፡ ሆኖም ያለ አንዳች አገልግሎት ነው ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያሳለፈው፡፡
ከኮምቦልቻ- ወልዲያ-ሃራ ገበያ ያለው ሁለተኛው የመስመሩ የግንባታ ምዕራፍ ደግሞ 122 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዙ ችግሮች ተጓቶ ቢቆይም አሁን ግን ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ተቀርፈው ያለምንም ችግር በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
83 በመቶ ያህል መጠናቀቁንም ነው ስራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
ከሀራ-ጃሮታ-ሀይቅ ከተማ ያለው የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ ተጠናቋልም ብለዋል የግንባታው አካል የሆኑ ዋሻዎች እና ድልድዮች ግንባታ መጠናቀቁን የገለጹት ኢንጂነር አብዱልከሪም፡፡
ሆኖም በሁለተኛ የግንባታው ምዕራፍነት የተያዘው ይህ ፕሮጀክት ልክ እንደ ቀዳሚው ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው መስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡