ኢትዮጵያ፤ ኬንያ የኤሌክትሪክ መስመር ፈትሻ ስትጨርስ የኃይል ሽያጭ እንደምትጀምር ገለጸች
የኢትዮ- ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ድርድር በስምምነት ተጠናቋል
በስምምነቱ ኢትዮጵያ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ትሸጣለች
ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ሲደረግ የነበረው የኤሌክትሪክ ሽያጭ ድርድር ትናንት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኬንያ ኤሌክትሪክ፣ መብራትና ኃይል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጂነር ጎፌሪ ሙሊ ተፈራርመዋል፡፡
- ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ለሶስት ጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ልትሸጥ ነው
- ኢትዮጵያ፤ሱዳን ያለባትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍል ጠየቀች
በዚህ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) መገኘታቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ኃላፊ፤ ኬንያ የኤሌክትሪክ መስመር ፈትሻ ስትጨርስ የኃይል ሽያጭ እንደሚጀመር ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ አሁን ላይ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ እንደምትሸጥም ተገልጿል፡፡ በቀጣይ ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን እስከ 400 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ነው ተቋሙ ያስታወቀው፡፡
ኢትዮጵያ ፤ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል መሸጥ የምትጀምረው ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ መሆኑንም አቶ ሞገስ መኮንን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ሽያጩ የሚጀመረው ኬንያ የኤሌክትሪክ መስመር ፍተሻ ካደረገች በኋላ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞገስ በኢትዮጵያ በኩል ፍተሻ ተደርጎ ማለቁን አስታቀውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመስመር ፍተሻ ያደረገችው ከሁለት ዓመት አስቀድሞ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የኬንያ ግን አሁን ከስምምነት በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ እያካሄደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ስምምነት መፈረሟ ይታወሳል፡፡