በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሳተፍ ጨረታውን ያሸነፈው ኩባንያ የሚጠበቅበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አደረገ
ጨረታውን ያሸነፈው ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደርጋል
ሁለተኛውን የቴሌኮም ኦፕሬተር ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል
በኢትዮጵያ በግል የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ዘርፍ ለመሳተፍ ጨረታውን ያሸነፈው ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ያሸነፈበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ለመንግስት ገቢ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ እንዳሉት በጨረታ ሰነዱ በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረት 14 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኩባንያው ጨረታውን ያሸነፈበትን ዋጋ ለመንግስት ገቢ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በዚህም መሰረት ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ያሸነፈበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ለመንግስት ገቢ ማድረጉን ኢንጂነር ባልቻ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት ለጨረታው ማስኬጃ ከእንግሊዝና ከአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማት 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር አግኝቷል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ሁለተኛውን የቴሌኮም ኦፕሬተር ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በጨረታው ላይ አዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ዕድልም ሊታይ ይችላል ብለዋል።
ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስ ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመቅረጽ ሲተገብራቸው ከነበሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጉዳዮች መካከል በመንግስት ብቻ ተይዘው የነበሩ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረግ ስራዎች ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ አንዱ በቴሌኮም አገልግሎት ልምድና አቅም ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ለማስቻል ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶ ሲሰራ የነበረው ስራ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ከአንድ ዓመት በፊት ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ለቀረበው ጥሪ የጨረታ ሰነዱን ከገዙ ዘጠኝ ድርጅቶች መካከል ሁለት ኩባንያዎች መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ ከነዚህም መካከል ፣ Vodafone, Vodacom, Safaricom, Sumitomo Corporation, and the CDC Group የተባሉ ዓለምአቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በጥምረት ያቋቋሙት ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ (Global partnership for Ethiopia) ማሸነፉ ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ምይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡