በትግራይ ክልል የቴሌኮም አገልግሎትን ለማስቀጠል ከመንግስትና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገርኩ ነው- ኢትዮ ቴሌኮም
ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ ከባድ ችግሮች ገጥመውት እንደነበረም አስታውቋል
ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት ዓመት 56.5 ቢሊየን ብር ማግኘቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል
የኢትዮ ቴለኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ በ2013 በጀት ዓመት የተቋሙ አፈጻጸም ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት 56.5 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ይህም ከእቅዱ አንጻር ሲታይ፣ 101.7 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በውጭ ምንዛሪም 166.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማስገባቱን በመግለጽ፤ ከእቅዱ 106 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመግለጫቸው አክላም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ ክልል ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በቴሌኮም መሰረት ልማት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።
በሰሜን ሪጅን የቴሌኮም አገልግሎትን ለማቅረብ በክልሉ ያሉ 652 ቢቲኤስ ማሰራጫዎችን ለመጠገን፣ ሀይል አቅርቦት እንዲያገኙ ለማድረግ እና ጄኔሬተሮችን ነዳጅ መሙላት ያስፈልጋል ብለዋል።እንዲሁም ደንበኞች የአየር ሰዓት መግዛት እንዲችሉ የአየር ሰዓት የሚያከፋፍሉ የኢትዮ ቴሌኮም ወኪሎች ጋር የአየር ሰዓት መላክ እና ገንዘብ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም በተወሰነ ደረጃ ጥገናዎችን በማከናወን አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበረም አስታውሰዋል።
ሆኖም ግን በቅርቡ በድጋሚ በተፈጠረው ችግር በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስጀመር ስራውን ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር ስለሚሰራ የቴሌኮም አገልግሎትን ለማስቀጠል አስቸጋሪ እንደሆነበት አንስተዋል።
አሁን ላይ ተቋሙ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና ባለድርሻ አካላት ጋር የቴሌኮም አገልግሎቱን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል የሚለው ላይ እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ ያሉ የተቋሙ ሰራተኞች ለጥገና፣ አገልግሎት ለመስጠት እና መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታን ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ደንበኞች የሚፈልጉትን የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት ባመለቻላቸው ቅር የተሰኙ ደንበኞች መኖራቸውን ገልጸው፤ ደንበኞች ተቋሙ የገጠሙትን ተግዳሮቶች እንዲረዱለት ጠይቀዋል።
ከሰሜን ሪጀን ውጪ ኢትዮ ቴሌኮም ከፀጥታ ችግረ ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ ከባድ ተግዳሮት ገጥመውት ነበረ ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ብዙ ዋጋም ተከፍሎ መሰረተ ልማቶች እየተጎዱ፣ ሠራተኞች ላይ ጉዳት እየደረሰ በርካታ ቦታዎች ላይ በእጀባ ጭምር ሥንሰራ ነበር ብለዋል።
አሁን ላይ ግን ቀደም ካለው ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተው፤ ወደፊትም ህብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ ከመንግስት እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካልት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በተገባደደው በጀት ዓመት ከጽጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ በቢሊየን የሚገመት ገቢ እንዳጣም በማስታወስ፤ በተለይም በሰሜን ሪጅን የተዘረጋው መሰረት ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ መተመኑንም ጠቅሰዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪም ሌላ ገለልተኛ አካልም ምን ያክል ጉዳት እንደደረሰ በማጥናት ጉዳቱ መጠን በገንዘብ መተመኑንም አስታውቀዋል።