የኢትዮጵያ የደህንነት ተቋማት ከአፋር የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በጋራ በተሰራ ኦፕሬሽን ወታደሮቹ ነጻ መውጣታቸው ተገልጿል
ኢትዮጵያ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ የጅቡቲ ወታደሮችን ማስለቀቋን ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳሳወቀው በፈረንጆቹ ጥቅምት 6 ቀን 2022 ላይ የጅቡቲ ጦር ማዕከል ከሆነው ልዩ ቦታው ጋራብቲሳን ማዘዣ በታጣቂዎች ጥቃት ደርሶበት ነበር።
ታጣቂዎቹ በወቅቱ ስድስት የጅቡቲ ጦር አባላትን አግተው ወስደዋል የተባለ ሲሆን እነዚህ ወታደሮች ለጅቡቲ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸው ተገልጿል።
በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ፍስሀ ሻወል በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ የጽጥታ እና ደህንነት ባለሙያዎች ከአፋር የሀይማኖት አባቶች ጋር በመቀናጀት በተሰራ ኦፕሬሽን ወታደሮቹን ከታጣቂዎቹ ማስለቀቅ ተችሏል።
በአፋር ክልል ታንደም በተባለ ስፍራ እንደተካሄደ በተገለጸው በዚህ ኦፕሬሽን ነጻ የወጡት ወታደሮችም ለጅቡቲ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ድርጊቱ የኢትዮጵያን እና ጅቡቲን ወዳጅነት ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ከአንድ ወር በፊት ወታደራዊ ትብብርን ጨምሮ በብዙ የጋራ ጉዳዮች በጋር ለመስራት አዲስ ስትራቴጂካዊ ስምምነት በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ይህን ስትራቴጂካው ስምምነትንም የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ከጅቡቲ አቻቸው ጋር ተፈራርመዋል።