ደቡብ ሱዳን ነዳጅ ወደ ውጭ ለመላክ ጅቡቲ ወደብ ላይ ቦታ መግዛቷ አስታወቀች
የደቡብ ሱዳን መንግስት የነዳጅ ሚኒስትር ከፖርት ሱዳንና ሞምባሳ በተጨማሪ ጅቡቲን እንጠቀማለን ብለዋል
ደቡብ ሱዳን አሁን ላይ ነዳጅ የምትልከው “ፖርት ሱዳንን በመጠቀም ብቻ” መሆኑ ይታወቃል
ደቡብ ሱዳን ድፍድፍ ዘይትን ወደ ውጭ ለመላክ የጅቡቲ ወደብ እንደ አማራጭ መጠቀም እንደምርፈልግ አስታወቀች፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት የነዳጅ ሚኒስትር ፉት ካንግ ኩል በነዳጅ ጉዳይ እየመከረ ባለውና የጅቡቲው የኢነርጂ እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ዩኑስ አሊ ጌዲ በተገኙበት የጁባው ኮንፈረንስ እንደተናገሩት ደቡብ ሱዳን ነዳጅን ወደ ውጭ ለመላክ እና እቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በጅቡቲ ወደብ ላይ 12 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ገዝታለች ብሏል፡፡
“እኛ ፖርት ሱዳን እና ሞምባሳን ብቻ ስንጠቀም ቆይተናል ነገር ግን በቅርቡ ወደ ጅቡቲ ለመሄድ ወስነናል” ሲሉም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋ ለአል ዐይን አማርኛ እንደናገሩት “በሞምባሳ በኩል ነዳጅ መላክ አንችልም፤ ስለዚህም ጅቡቲን መጠቀም ግድ ይለናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ነዳጅ ለመላክ መሰረተ ልማት ወሳኝ በመሆኑ በቅድሚያ “ከደቡብ ሱዳን-አትዮጵያ እስከ ጅቡቲ የሚያገናኘው መስመር መዘርጋት አለበት”ም ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
ደቡብ ሱዳን፤ በሱዳን የተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ ፖርት ሱዳንን በመጠቀም ነዳጅ ወደ ውጭ ሀገራት መላኳ ለማቆም ተገዳ የነበረ ቢሆንም፤ አንጻራዊ ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎ አሁን ፖርት ሱዳን ብቸኛ ነዳጅ የምትልክበት ወደብ አድርጋ በመጠቀም ላይ ትገኛለች፡፡
ደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚዋ በነዳጅ ንግድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ይታወቃል፡፡