የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ
አየር መንገዱ ወደ ትግራይ ክልል ኤርፖርቶች በረራ አቁሞ ቆይቷል
የፌደራል መንግሥት እና ህወሀት የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት በመመለስ ላይ ናቸው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።
በሰሜን ኢትዮጵያ በህወሀት እና የፌደራል መንግሥቱ አማካኝነት ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ነበር አየር መንገዱ መደበኛ በረራውን ያቋረጠው።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው በዚህ ጦርነት የባንክ፣ ቴሌኮሙንኬሽን እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችም የሀገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌ ገብቶ ከቆየባቸው ጥቂት ወራት በስተቀር አገልግሎቶቹ ተቋርጠው ቆይተዋል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ በተደረሰ ስምምነት መሰረት ህወሀት እና የፌደራል መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል።
ይሄንን ስምምነት ተከትሎም መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች ዳግም በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
ከነዚህ መካከልም አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን ከነገ ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ከአዲስ አበባ መቐለ መደበኛ በረራውን እንደሚጀምር አስታውቋል።
በትናንትናው ዕለትም በአፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግሥት ልዑካን ወደ መቀሌ አምርቶ ከተለያዩ አመራሮች እና የህዝብ ወኪሎች ጋር ተወያይቶ መመለሱ ይታወሳል።
በውይይቱ ወቅትም የባንክ፣ ትራንስፖርት ፣ ቴሌኮሙንኬሽን እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡ ተገልጿል።