በኢትዮጵያ የበረራ ደህንነት ችግር አለመኖሩን የአቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ
አሜሪካ ከቀናት በፊት አዲስ አበባን ጨምሮ የበረራ ደህንነት ችግር እንዳለ አስጠንቅቃ ነበር
ባለስልጣኑ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሁሉም ኤርፖርቶች እና የአየር ክልሎች የበረራ ደህንነት አስተማማኝ መሆኑን አስታውቋል
በኢትዮጵያ የበረራ ደህንነት ችግር አለመኖሩን የኢትዮጵያ ሲቪል የአቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የአሜሪካ ፌደራል አቬሽን ባለስልጣን ከሁለት ቀናት በፊት አዲስ አበባን ጨምሮ የበረራ ደህንነት ችግር ስላለ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ አስጠንቅቆ ነበር፡፡
ባለስልጣኑ በድረገጹ ባወጣው ማስጠንቀቂያ በኢትዮጵያ ባሉ ኤርፖርቶች አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፕላን ጣቢያዎች የበረራ ደህንነት ችግር አለ ብሎ ነበር፡፡
በርካታ ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃንም የአሜሪካውን ተቋም ዋቢ አድርገው የበረራ ደህንነነቱ ችግር እንደሚኖር ዘግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዛር ባወጣው መግለጫ መረጃው ትክክል አለመሆኑን እና አገልግሎቱ አሁንም መቀጠሉን አስታውቋል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ሁሉም ኤርፖርቶች እና የአየር ክልል ከበረራ ደህንነት ስጋት ነጻ ናቸው ብሏል፡፡
ባለስልጣኑ ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጾ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ዓለም አቀፉ የበረራ ደህንነቶችን ባሟላ መልኩ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
የአሜሪካ መንግስት፣ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ ተለዋዋጭ መሆኑን በተደጋጋሚ በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ዜጎቿ በተገኘው አማራጭ ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቧ ይታወሳል፡፡