የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኑን ዳግም ወደ በረራ መመለሱን አስታወቀ
36 የሚሆኑ የአለም አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት መልሰዋል
አውሮፕላኑ በሌሎች ሀገራት ወደ በረራ ከተመለሰበት 1 ዓመት ወዲህ በአጠቃላይ 349 ሺህ በረራዎችን አድርጓል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኑን ዳግም ወደ በረራ መመለሱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላት፣ የቦይንግ የስራ ኃላፊዎች፣ ሚኒስትሮች፣አምባሳደሮች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ደንበኞች በዚህ የመጀመሪያ በረራ ላይ ታድመዋል።
አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ወደ አገልግሎት መመለስ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ “የበረራ ደህንነት የአየር መንገዳችን ተቀዳሚና ወሳኝ ጉዳይ ነው፤ እያንዳንዷ የምንሰራት ስራና የምንወስናት ውሳኔ በበረራ ደህንነት አብይ ጉዳይ የተቃኘ ነው፣ በዚህ መርህ ላይ በመመስረት ነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላናችንን ወደ አገልግሎት የመለስነው" ብለዋል።
የፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን /FAA/፣ የአውሮፓ ህብረት የአቪየሽን ደህንነት ኤጀንሲ /EASA/፣ ትራንስፖርት ካናዳ፣ የቻይና ሲቪል አቪየሽን አስተዳደር /CAAC/፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን /ECAA/ እንዲሁም ሌሎች የአቪየሽን ተቆጣጣሪ አካላት ለአውሮፕላኑ ምስክርነትና ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን፣ 36 የሚሆኑ የአለም አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት መልሰዋል።
የማክስ አውሮፕላን ሞዴል ዳግም ወደ በረራ ከተመለሰበት አንድ ዓመት ወዲህ በአጠቃላይ 349 ሺህ በረራዎችን ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም ወደ 900 ሺህ የሚደርስ የበረራ ሰአት አስመዝግቧል።
ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢንዶኔዥያ ላየን አየር መንገዶች የሖኑ ሁለት ማክስ አውሮፕላኖች ከሶስት አመት በፊት ተከስክተው በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
አውሮፕላኖቹ አሁን ላይ ግን ተገቢው የደህንነት ማስተካከያ ተደርጎላቸው በመላው አለም በዳጋም በረራ ላይ ይገኛሉ።