ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ20 ዓመታት በኋላ በ2011 ዓ.ም የአየር ትራንስፖርት መጀመራቸው ይታወሳል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋርጦ የነበረው የአዲስ አበባ አመራ በረራ ዳግም መጀመሩን አስታወቀ።
ከአዲስ አበባ አስመራ እና ከአስመራ አዲስ አበባ የሚደረገው በረራም በዛሬው እለት መጀመሩንም ነው አየር መንገዱ በፌስ ቡክ ገጹ ያስታወቀው፡፡
የኤርትራ ትራንስፖርት እና ኮሙንኬሽን ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ባወጣው መረጃ መሰረት በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ወደ ሀገሯ እና ከአስመራ ወደ ሌሎች ሀገራት ይደረጉ የነበሩ በረራዎችን አግዳ ነበር።
በዚህም ከአስመራ ወደ አዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የሚደረጉ በረራዎች ተቋርጦ እንደቆየም ይታወቃል።
ኤርትራ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አቁማው የነበረውን ዓለም አቀፍ በረራ በድጋሚ መጀመሯን ተከትሎም ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አመራ የሚያደርገውን በረራ የጀመረው።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ20 ዓመታት በላይ ምንም አይነት የትራንስፖርት ግንኙነት ያልነበራቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በ2011 ዓ.ም የአየር ትራንስፖርት መጀመራቸው ይታወሳል።
በወቅቱ የመጀመሪያውን በረራው ወደ አስመራ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ዘመናዊ አውሮፕላን 250 ገደማ ሰዎችን ይዞ ወደ ኤርትራ መጓዙም አይዘነጋም።