የ2015 የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ
የተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛው በአዲስ አበባ ሲመዘገብ የማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ በአማራ ክልል ተመዝግቧል
የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ከአምናው ጋር ተቀራራቢ ነው ተብሏል
በ2015 የ12ኛ ክፍል ፈተና 649 ከፍተኛው ውጤት መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የ2015 የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት በ2015 ዓ.ም 845 ሺህ ተማሪዎች ፈተናው ላይ ተቀምጠው የማለፊያ ውጡ ወይም ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ብዛት 27 ሺህ 267 ብቻ ናቸው የተባለ ሲሆን 19 ሺህ 17 ከተፈጥሮ ሳይንስ 8ሺህ 250 ተማሪዎች ደግሞ ከማህበራዊ ሳይንስ ናቸው ተብሏል፡፡
649 የተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛው ውጤት ሆኖ ሲመዘገብ በአዲስ አበባ ልደታ የሚገኝ ትምህርት ቤት ከፍተኛውን ውጤት ሲያስመዘገብ የማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533 በአማራ ክልል ሐዲስ ዓለማየሁ ትምህርት ቤት መመዝገቡ ተገልጿል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሀኑ በመግለጫቸው አክለውም አምስት ትምህርት ቤቶች ሁሉንም ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች አሳልፈዋል የተባለ ሲሆን 1ሺህ 326 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ አላሳለፉም ብለዋል፡፡
በደብረ ማርቆስ የሚገኘው ሐዲስ አለማየሁ ትምህርት ቤት፣ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ባህርዳር ስቴም ትምህርት ቤት፣ ሀይራንዜ ትምህርት ቤት፣ ጎጎ ትምህርት ቤት፣ ኦዳ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ኮተቤ ዩንቨርሲቲ ትምህርት ቤት፣ የኔታ አካዳሚ ፣ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት እና ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ባሳለፏቸው ተማሪዎች ብዛት ምርጥ የኢትዮጵያ 10 ትምህርት ቤቶች ተብለዋል፡
ተማሪዎች ውጤታቸውን ከነገ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ በፈተናዎች ኤጀንሲ ድረገጽ ላይ እየገቡ ማየት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
የ2ዐ15ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች መስከረም 29, 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚከተሉት አማራጮች ውጤታቸውን ማየት ይችላሉ
በዌብ ሳይት
https://eaes.edu.et/
በአጭር የጽሑፍ መልዕክት
6284
በቴሌግራም
https://t.me/eaesbot
ከማታ ትምህርት 16 ሺህ ተፈታኞች ውስጥ ያለፉት 12 ተማሪዎች ብቻ ናቸው የጠባለ ሲሆን አጠቃላይ ውጤቱ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ብዙ መሻሻሎች እንዳልታዩ ተገልጿል፡፡
አምና በልዩ ሁኔታ የተጀመረው የሬሚዲያል ፕሮግራም እድል ዘንድሮም እንደሚቀጥል ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡