የ12ኛ ክፍል ፈተና ማለፊያ ነጥብ ይፋ ሆነ
ውጤቱ በመጀመሪያው እና ሁለተኛው ዙር ተፈታኞች የመግቢያ ውጤቱ የተለያየ እንደሆነም ተገልጿል
መግቢያ ነጥቡ በመንግስት እና በግል ዩንቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን ይመለከታል
የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ማለፊያ ነጥብ ይፋ ሆነ።
የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ለጋዜጠኞች የ12ኛ ክፍል መለቀቂያ ፈተና መቁረጫ ነጥብ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በሁለት ዙር ለተሰጠው የመልቀቂያ ፈተና የተሰጠው የማለፊያ ነጥብ የተለያየ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም መሰረት በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ለመማር ለተፈጥሮ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞች ማለፊያ ነጥብ ለወንድ 363 ለሴት 351 ሲሆን በተፈጥሮ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ለወንድ 351 ለሴት 339 ማለፊያ ነጥብ መሆኑ በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
ለተፈጥሮ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታ የማለፊያ ነጥብ 300 ሆኗል።በተፈጥሮ ሳይንስ ድጋሜ ተፈታኞች ማለፊያ ነጥብም 380 ሆኖ መቆረጡ ተገልጿል።
በመጀመሪያው ዙር የተፈተኑ እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል የተፈጥሮ ሳይንስ መቁረጫ ነጥብ 300 ሆኗል።
ለማህበራዊ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ ለወንድ 264፣ ለሴት 254 ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ለወንድ 254፣ ለሴት 250 ማለፊያ ነጥብ ሆኖ ተቆርጧል ተብሏል።
ለማህበራዊ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታዎች ማለፊያ ነጥብ 250 መሆኑን እና በማህበራዊ ሳይንስ ድጋሜ ተፈታኞች ለሁለቱም ፆታ የማለፊያ ነጥብ 280 እንደሆነ ተገልጿል።
በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል የማህበራዊ ሳይንስ መቁረጫ ነጥብ 250 ሆኗል።
በሁለተኛ ዙር ፈተናቸውን የወሰዱ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማህበራዊ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞች ውጤትም ይፋ የሆነ ሲሆን በዚህም መሰረት በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ለመማር ለተፈጥሮ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞት ማለፊያ ነጥብ ለወንድ 423 ለሴት 409 ሲሆን በተፈጥሮ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ለወንድ 410 ለሴት 396 ማለፊያ ነጥብ መሆኑ ተገልጿል።ለተፈጥሮ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታ የማለፊያ ነጥብ 350 ሆኗል። በተፈጥሮ ሳይንስ ድጋሜ ተፈታኞች ማለፊያ ነጥብም 443 ሆኖ መቆረጡ ተገልጿል።
በሁለተኛ ዙር የተፈተኑ እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል የተፈጥሮ ሳይንስ መቁረጫ ነጥብ ከ350 በላይ መሆኑ ተነግሯል።
ለማህበራዊ ሳይንስ መደበኛ ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ ለወንድ 317፣ ለሴት 305 ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ በታዳጊ ክልሎች እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላሉ መደበኛ ተፈታኞች ለወንድ 305፣ለሴት 300 ማለፊያ ነጥብ ሆኖ ተቆርጧል።
ለማህበራዊ ሳይንስ መስማት ለተሳናቸው ሁለቱም ፆታዎች ማለፊያ ነጥብ 300 መሆኑን እና በማህበራዊ ሳይንስ ድጋሜ ተፈታኞች ለሁለቱም ፆታ የማለፊያ ነጥብ 335 እንደሆነ ተገልጿል።
በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለመከታተል የማህበራዊ ሳይንስ መቁረጫ ነጥብ ከ 300 በላይ መሆኑም ተገለጿል።
ውጤቱ ለመጀመርያ ዙር ተፈታኞች ለተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 እዲሁም ለማህበራዊ ሳይንስ ከ500 የተያዘ መሆኑን እና በሁለተኛ ዙር ተፈታኞች ለተፈጥሮ ሳይንስ ከ700 እንዲሁም ለማህበራዊ ሳይንስ ከ600 የተያዘ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።