በቱርክ አንካራ ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድርድር ለምን ተራዘመ?
አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ተደርገው ተሾመዋል
የቀድሞው ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ምክንያት ተወካይ ሆነዋል
በቱርክ አንካራ ሊካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድርድር ለምን ተራዘመ?
ላለፉት አራት ዓመታት በአልጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደእ የነበሩት ነቢያት ጌታቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ሆነው ተሹመዋል።
አምባሳደር ነቢያት በዛሬው ዕለት ከውጭ ጉዳይ እና ዲፕሎማሲ ቋሚ ዘጋቢ ከሆኑ ጋዜጠኞች ጋር ተዋውቀዋል።
አምባሳደር ነቢያት ከአራት ዓመት በፊት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የአሁኑ ሹመት ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።
አምባሳደር ነቢያት የተኳቸው የቀድሞው ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በአፍሪካ ህብረት እና በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምክትል የኢትዮጵያ ተወካይ ተደርገው መሾማቸውን ከሚንስቴሩ ሰምተናል።
ትውውቅ ላይ ባተኮረው የዛሬው እና የመጀመሪያ የውጭ ጉዳይ እና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች መግለጫ ላይ ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ነበር።
ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ደህንነት ፣ የኢትዮጵያ-ኤርትራ ግንኙነት ምን ላይ ነው? የግብጽ ኤርትራን እና ህወሀትን ላደራድር ማለቷ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ሊባል አይችልም? የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የአንካራ ድርድር ለምን ተራዘመ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
አምባሳደር ነቢያት በምላሻቸው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አንካራ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ሶስተኛው ዙር ድርድር በተመድ ጉባኤ ምክንያት የስራ መደራረብ በማጋጠሙ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ከታደሰበት 2018 ጀምሮ በመልካም ሁኔታ ላይ መቀጠሉን የተናገሩት ቃል አቀባዩ በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ቤሩት ያለው የኢትዮጵያ ቆንስላ እና በዋናው መስሪያ ቤት በኩል ድጋፍ እና ክትትል በመደረግ ላይ መሆኑንም በምላሻቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ይሁንና ግብጽ ኤርትራን እና ህወሀትን አስታርቃለሁ ማለቷ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ሊሆን አይችልም? እንዲሁም ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የወደብ ስምምነት ከተገበረች አማጺያንን አስታጥቃለሁ ማለቷ ዙሪያ የኢትዮጵያ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።