ቱርክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለሶስተኛ ጊዜ ድርድር ከማድረጋቸው በፊት በተናጠል ለማናገር ማቀዷን ገለጸች
ባለፈው ማክሰኞ እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረው ሶስተኛ ዙር ንግግር ተሰርዟል
የቱርስ ውጭ ጉዳየሰ ሚኒስትር አክለውም ሁለቱ አካላት "በተወሰኑ ነጥቦች ወደ አንድ ስለመጡ" መፍትሄ ይገኛል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል
ቱርክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለሶስተኛ ጊዜ ድርድር ከማድረጋቸው በፊት በተናጠል ለማናገር ማቀዷን ገለጸች።
ቱርክ በኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ መካከል በተፈረመው የወደብ ስምምነት ምክንያት አለመግባባት ውስጥ የገቡትን አዲስ አበባን እና ሞቃዲሹን ለሶስተኛ ጊዜ ድርድር ከማድረጋቸው በፊት በተናጠል የማናገር እቅድ እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀካን ፊዳን በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
በፈረንጆቹ አዲስ አመት የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያዊ በኤደን ባህረ ሰላጤ 25 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ለ50 አመት በሊዝ እንድትይዝ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ እንደሚያስችል ተገልጾ ነበር።
ነገርግን ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድጋ የምታየው ሶማሊያ ስምምነቱን ሉኣዊነቷን እና አለምአቀፍ ህግን ይጥሳል በሚል በጽኑ ተቃወመችው።
ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር እስከማባረር የደረሰ እርምጃ በመውሰድ አለመግባባቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጋዋለች።
ቱርክ የተበላሸውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለመጠገን እስካሁን ሁለት ዙር ንግግሮችን አዘጋጅታለች። ባለፈው ማክሰኞ እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረው ሶስተኛ ዙር ንግግር ተሰርዟል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቱርክ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በሚኒስትር እና በመሪዎች ደረጃ ማናገሯን እንደምትቀጥል መግለጻቸውን ሮይተርስ የቱርኩን አናዶሉ የዜና ወኪል ጠቅሶ ዘግቧል።
ሚኒስትሩ አክለውም ሁለቱ አካላት "በተወሰኑ ነጥቦች ወደ አንድ ስለመጡ" መፍትሄ ይገኛል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ዙር ንግግሮች ትምህርት መወሰዱን የገለጹት ሚኒስትሩ ሁለቱን አካላት ለቀጥተኛ ንግግር ወደ አንካራ ከመጋበዝ ይልቅ አቋማቸው ወደ አንድ እስከሚመጣ ድረስ በተናጠል ለማናገር ማለማቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ነሐሴ ወር ሁለተኛ ዙር ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ ቱርክ እና የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰጡት መግለጫ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ ባይደርሱም መሻሻሎች መኖራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል
ከዚህ ንግግር መጠናቀቅ በኋላ በቀጣናው አዳዲስ ሁነት ተከስቷል።
ግብጽ ወደ ሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላካ እና አዲስ የሚቋቋመው የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ወታደር የማዋጣት ፍላጎት እንዳላት ተዘገበ።
ኢትዮጵያዊ ስለጉዳዩ በቀጥታ ባትጠቅሶም ሶማሊያን የሚከስ መግለጫ አወጣች።
ሶማሊያ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራች መሆኑን እና ይህንን ተግባር በዝምታ እንደማታልፈው ኢትዮጵያ አስጠነቀቀች። ይህን ተከትሎ ነው ሶስተኛው ዙር ንግግር የተሰረዘው።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው እለት በሰጠው መግለጫ የታቀደው ንግግር የተሰረዘው በፕሮግራም መደራረብ ምክንያት ነው ብሏል።
አደራዳሪዋ ቱርክ እና ሶማሊያ ግን ለምን እንደተሰረዘ ያሉት ነገር የለም።