ሶማሊያ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ እየገባ ነው አለች
ሚኒስቴሩ ይህ ድርጊት የሶማሊያን ሉአላዊነት የሚጥስ እና ቀጣናዊ የደህንነት አንድምታ ያለው ከባድ ጥሰት ነው ብሏል
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና የአለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾች በኢትዮጵያ ግዛት በኩል ወደ ፑንትላንድ መግባታቸውን እንደሚያወግዝ ገልጿል
ሶማሊያ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ እየገባ ነው አለች።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና የአለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾች በኢትዮጵያ ግዛት በኩል ወደ ፑንትላንድ መግባታቸውን እንደሚያወግዝ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ይህ ድርጊት የሶማሊያን ሉአላዊነት የሚጥስ እና ቀጣናዊ የደህንነት አንድምታ ያለው ከባድ ጥሰት ነው ብሏል።
የጦር መሳሪያ የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች ያለምንም ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እና ማጣራት ከኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ መግባታውን ማረጋገጡን የገለጸው ሚኒስትሩ የሶማሊያ ሉአላዊነት መጣሱን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብሏል።
ይህ ክስተት ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ጋልሙዱጉ እና በጦር ጄት ወደ ጎዴ ማጓጓዟን የሚያሳይ ነው ያለው ሚኒስቴሩ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላም ስለሚያናጋ ይህ ተግባር መቆም አለበት ሲል አሳስቧል።
ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ በይፋ የሰጠችው መልስ የለም።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በፈረንጆቹ ጥር 1፣2024 የወደብ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ወደ ከረረ ዲፕሎማሲያዊ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህር ሰላጤ ለንግድ እና ለባህር ኃይል መቀመጫ የሚሆን 2ዐ ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ በሊዝ ኪራይ ለ50 አመታት እንድትጠቀም እና በምላሹ ለሶማሊያ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ ያስችላል ተብሎ ነበር።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ የምታያትን ስማሊያን አስቆጥቷል። ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር አባረረች፣ በግዛቷ አልሸባብን ለአስርት አመታት ሲዋጋ የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለማስወጣት ዛተች።
ይህም ሆኖ ሁለቱ ሀገራት ችግሩን በንግግር ለመፍታት በቱርክ አማካኝነት በተናጠል ሁለት ጊዜ ንግግር አድርገዋል። ባለፈው ማክሰኞ ሊካሄድ የነበረው ሶስተኛ ዙር ድርድር ተሰርዟል።
ሁለተኛው ዙር ንግግር ባለፈው ነሐሴ ወር ከተጠናቀቀ በኋላ በቀጣናው ውጥረት የሚያባብስ አዲስ ሁነት ተፈጠረ።
ግብጽ ወደ ሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላካ እና አዲስ የሚቋቋመው የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ወታደር የማዋጣት ፍላጎት እንዳላት ተዘገበ።
ኢትዮጵያዊ ስለጉዳዩ በቀጥታ ባትጠቅሶም ሶማሊያን የሚከስ መግለጫ አወጣች።
ሶማሊያ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራች መሆኑን እና ይህንን ተግባር በዝምታ እንደማታልፈው ኢትዮጵያ አስጠነቀቀች።