በቢሾፍቱ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የኤሌክትሪክ ችግር እንዳለበት አስቀድሞ ይታወቅ ነበር ተባለ
የአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ ቦይንግ 737 ማክስ 8 የተሰኘው ምርቱ ችግር እንዳለበት አያወቀ ዝምታን መርጧል ተብሏል
መጋቢት 2011 ዓ.ም በተፈጠረው በዚህ አደጋ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ይጓዙ የነበሩ 157 ሰዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም
ከአራት ዓመት በፊት በቢሾፍቱ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የኤሌክትሪክ ችግር እንዳለበት አስቀድሞ ይታወቅ ነበር ተባለ፡፡
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ረፋድ ላይ መነሻውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ መዳረሻውን ደግሞ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አድርጎ በረራ የጀመረው ET-302 መሬት በለቀቀ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ቢሾፍቱ ልዩ ስፍራው ቱሉ ፎራ በተባለ ቦታ ነበር የተከሰከሰው።
የቦይንግ ኩባንያ ምርት የሆነው አውሮፕላኑ የበረራ ክፍል አባላቱን ጨምሮ 157 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር።
በአደጋው ሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን የአደጋው መነሻ የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ባጠናው የምርመራ ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል።
ቦይንግ ኩባንያ መጀመሪያ ላይ ለአደጋው ሃላፊነት እንደማይወስድ የገለጸ ቢሆንም ዘግይቶ ግን ኩባንያው ጥፋቱን በማመን ለተፈጠረው አደጋ ሀላፊነት እንደሚወስድ ገልጿል።
ቢቢሲ ዋቢ ያደረጋቸው የቀድሞ የቦይንግ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ግን የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮቹ ላይ እክል እንነበረበት ቦይንግ አስቀድሞ ያውቅ እንደነበር ተናግረኣል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የህይወት ዘመን ሽልማት አበረከቱ
የቀድሞው ስራ አስኪያጅ የሚመሩት ፋውንዴሽን ፎር አቪየሽን ሴፍቲ የተባለ ተቋም ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢንዴኔዢያ አየር መንገዶች የሆኑት 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከመከስከሳቸው በፊት የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ እክል እንደነበረባቸው ቦይንግ እያወቀ ዝም ማለቱን የሚጠቁም ነው፡፡
ከአደጋው በኋላም ኩባንያው አውሮፕላኑ የኤሌክትሪክ ችግር እንዳለበት የሚያሳየውን መረጃ መደበቁን ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ 737 ማክስ 8 አውሮፓላኖች በመላው ዓለም የበረራ አገልግሎት በመስጠት ለይ ሲሆኑ ተመሳሳይ አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በቢሾፍቱ በተፈጠረው አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል ዘጠኙ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ 32ቱ ኬንያዊያን፣ 18ቱ ካናዳዊያን፣ 8ቱ ቻይናዊያን፣ 7ቱ ፈረንሳውያን፣ 6ቱ ከግብጽ፣ 5ቱ ከሆላንድ እንዲሁም 4ቱ ከህንድ እንደሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።