የኤርትራ ሲቪል አቬሽን በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የበረራ ክልከላ መልሶ እንዲያጤነው እንጠይቃለን - የኢትጵያ አየር መንገድ
አየር መንገዱ የሀገሪቱ መንግስት በውሳኔው የሚጸና ከሆነ የሚጎዱት ወደ ኤርትራ የሚጓዙ መንገደኞች ናቸው ብሏል
ኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመስከረም 30 በኋላ ወደ አስመራ እንዳይበር መከልከሏ ይታወሳል
የኤርራ ሲቪል አቬሽን በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የበረራ ክልከላ መልሶ እንዲያጤነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መጠየቁን ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ ሲቪል አቬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚያደርገው በረራ ከመስከረም 30 / 2024 ጀምሮ እንዲቆም የሚያሳውቅ ደብዳቤ መላኩን ተከትሎ አየር መንገዱ ከአቬሽን ባለስልጣናቱ ጋር ለመናገገር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የኤርትራ ሲቪል አቭየሽን ውሳኔውን ሲያሳልፍ ወደ አስመራ በሚጓዙ ተጋዦች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ማንገላታት እንዲሁም ካሳ አለመክፈል የሚሉ ምክንያቶችን አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ በጉዳዩ ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከቅርብ ወራት በፊት ከኤርትራ ሲቪል አቬሽን የተሳፋሪዎች ሻንጣ ወደ ኋላ እየቀረ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቦ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ይህ የተፈጠረው ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ተጓዦች ብዙ ሻንጣ ስለሚይዙ እና ሁሉንም ማስተናገድ ባለመቻሉ በሚቀጥለው በረራ አየር መንገዱ ሻንጣዎችን ይልክ እንደነበር ነው ስራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ በፊት የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከ737 አውሮፕላን ውጪ ከፍ ያለ የመንገደኞች ማመላለሻ አውሮፕላን አየር መንገዱ እንዳይጠቀም እና በሳምንት ከ10 በረራ ውጪ እንዳያደርግ ተከልክሎ እንደነበር አንስተዋል፡፡
አቶ መስፍን አክለውም “የኤርትራ ተጓዦች ከሻንጣቸው ጋር እንዲጓዙ ለማስቻል የተሳፋሪዎችን ቁጥር በመቀነስ ተጓዦች ከሻንጣዎቻቸው ጋር እንዲጓዙ አድርገናል ከዚያ በኋላ ይህ ነው የሚባል ቅሬታ አልሰማንም ነበር” ብለዋል።
ሰኔ ላይ የሲቪል አቬሽኑ ለአየር መንገዱ በጻፈው ደብዳቤ በረራዎችን ወደ 15 እንድያሳድግና የሚጠቀመው የአውሮፕላን አይነት ላይ የነበረው ገደብ መነሳቱን ገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ አየር መንገዱ ባለበት የአውሮፕላኖች እጥረት ምክንያት በነበረው አሰራር መቀጠሉ ነው የተገለጸው፡፡
አሁን ላይ የወጣው ደብዳቤ ግን ከመስከረም 30/2024 በኋላ በረራ እንዳይደረግ የሚገልጽ ነው ያሉት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ይህን ተከትሎም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ክስ ቀርቦብናል፤ በዚህ በጣም አዝነናል ብለዋል፡፡
አክለውም “የኤርትራ ሲቪል አቬሽን አሁንም ውሳኔውን እንዲያጤነው እንጠይቃለን፤ ይህን የማይሆን ከሆነ የሚጎዱት ግን ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ተጓዦች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ ዳግም የጀመረው ከሁለት አስርት አመታት በኋላ በ2011 ዓ.ም ላይ እንደበረ ይታወሳል።
በወቅቱ የመጀመሪያውን በረራ ወደ አስመራ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ዘመናዊ አውሮፕላን 250 ገደማ ሰዎችን ይዞ ወደ ኤርትራ መጓዙም አይዘነጋም።