የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋሙን በተመለከተ በማህበራዊ ገጾች ላይ በተለቀቀው ቪዲዩ ዙሪያ ምን ምላሽ ሰጠ?
እንዲት ተሳፋሪ ከአውሮፕላኑ እንድትወርድ ስትጠየቅና ተሳፋሪዋ ስትከራከር የሚያሳይ ቪዲዮ በስፋት ተሰራጭቷል
“ጉዳዩት በጥልቀት ተመልክቻለው” ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በክስተቱ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰሞኑ ከአንዲት ተሳፋሪ ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ላይ በስፋት እየተዘዋወረ ስላለው ተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) ማብራሪያ ሰጥቷል።
ባሳለፍነው አርብ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ይደረግ የነበረ በረራ ላይ አንዲት መንገደኛ ከአውሮፕላን እንድትወርድና ከበረራ ላይ እንድትቀር ተደርጎ አንድ የመንግስት ሚኒስትር በቦታዋ እንደተተኩ ተደርጓል በሚል በአውሮፕላን ውስጥ የተቀረጸ ምስል በስፋት ተሰራጭቷል።
ኬንያዊ የሲንኤንኤን ጋዜጠኛ ላሪ ማዶዎ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ አንዲት ተሳፋሪ በአየር መንገዱ ሠራተኞች መካከል የሚደረግ የተካረረ ክርክርን የሚያሳይ ሲሆን፤ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ተሳፋሪዋ ከአውሮፕላኑ እንድትወርድ ሲጠይቁ እና ተሳፋሪዋ አልወርድም እያለች ከሰራተኞቹ ጋር ስትከራከር ያሳያል።
ይህንን ተከትሎ ወቀሳ የቀረበበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ በዛሬው እለት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው መግለጫው፤ ባሳለፍነው አርብ በሐምሌ 12 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ኬንያ በሚበረው ET308 አውሮፕላን ላይ ተሳፋሪ በግድ እንዲወርድ እንደተደረገ ተደርጎ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የተለቀቀውን ቪዲዮ ጊዜ ወስዶ በጥልቀት መመልከቱን በመግለጽ፤ የተለቀቀው ቪዲዮ እውነታውን የሚገልጽ እንደማይገልጽ አስታውቋል።
በእለቱ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለሚደረገው በረራ ትርፍ ትኬት መቆረጡን የገለጸው አየር መንገዱ፤ ተጠባባቂ ትኬት የያዙ ሶስት ተሳፋሪዎች አውሮፕኑ ሊነሳ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት መድረሳቸውን ተከትሎ የአየር መንገዱ ሰራኞች አውሮፕላኑ ስለሞላ መሳፈር እንደማይችሉ እና በቀጣይ በሚኖረው በረራ እንደሚጓዙ እንደነገሯቸው አስታውቋል።
ሆኖም ግን ተሳፋሪዎቹ በሰራተኞች የተነገራቸውን ምክር ወደ ጎን በመተው የደህንነት አባላትን በማለፍ አውሮፕላኑን ለመሳፈር በመሞከራቸው በፀጥታ አባላት እንዲወርዱ ተደርጓል ብሏል።
አየር መንገዱ አንዲት መንገደኛ ከአውሮፕላን እንድትወርድና ከበረራ ላይ እንድትቀር ተደርጎ አንድ የመንግስት ሚኒስትር በቦታዋ እንደተተኩ ተደርጓል በሚል የተሰራጨው መረጃም ትክክል አይደልም ብሏል።
በቪዲዮው ላይ ስትከራከር የምትታየው መንገደኛ ያዘችው ትኬት በኢኮኖሚ ክፍል መሆኑን ያስታወቀው አየር መንገዱ በቢዝነስ ክፍል ይበር ከነበረው እና ኢትዮጵያዊ ዜግነት ካለው መንገደኛ ጋር በምንም መልኩ አይገናኙም ሲል አስታውቋል።
ከመጠን በላይ ትኬት በመቆረጡ ሳቢያ በዕለቱ ተጠባባቂ ትኬት ይዘው በረራቸው የተስተጓጎለ ተሳፋሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በቀጣይ በረራ ወደ መዳረሻቸው እንዲጓዙ መደረጉንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞቹን ደህንነት ለመጠበቅ የተደነገገውን የአሠራር መመሪያ ለማክበር ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል።