ኢትዮጵያ ስደተኞች ስራ እንዲቀጠሩ እና እንዲነግዱ የሚያስችል መመሪያ አዘጋጀች
ወደ ኢትዮጵያ የገቡ እና ህጋዊ የሆኑ ስደተኞች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችለው ህግ የአፈጻጸም መመሪያ እየተዘጋጀለት ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በዚህ የጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች አፈጻጸም መመሪያ ላይ የህዝብ አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ብሏል
ኢትዮጵያ ስደተኞች ስራ እንዲቀጠሩ እና እንዲነግዱ የሚያስችል መመሪያ አዘጋጀች፡፡
አንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ያስጠለለችው ኢትዮጵያ እውቅና ያገኙ ስደተኞች ስራ መቀጠር የሚያስችላቸውን መመሪያ ማዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡
የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት እንዳስታወቀው በ2011 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ስራ መቀጠርን ጨምሮ ሌሎች ጥቅሞችን እንዲያገኙ የሚያደርገው ህግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን አስታውቋል፡፡
ይህ አዋጅ የተደነገገውን ዕውቅና ያገኙ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንዲሁም የተቀባይ ማህበረሰቦችን የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚል የተዘጋጀ ነውም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ከ10 ሺ በላይ ስደተኞች መመዝገባቸውን ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ ገለጹ
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትም የስደተኞችን የመስራት መብት ለማስፈፀም “ስደተኞች በስራ ላይ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመወሰን መመሪያ አዘጋጅቶ እንደነበር አስታውቋል፡፡
መመሪያ ቁጥር 02/2012 በሚል የተዘጋጀው ይህ ሰነድም የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1110/2010 የያዛቸውን መብቶች በሙሉ የያዘ ሆኖ እንደማይገኝም ተቋሙ ገልጿል።
የነበሩበትን ክፍተቶች በማረም በአዲስ መመሪያ መተካት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር፣ ከስራና ክህሎት ሚንስቴር እንዲሁም ከገቢዎች ሚንስቴር ጋር በጋራ አዲስ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጅቷል ተብሏል።
የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ዕውቅና ላገኙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ስለ ስራ ቅጥር፣ በንግድ ስራ ስለመሰማራት እና ስለግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በዝርዝር የሚገልጹ ድንጋጌዎችን በሚሸፍን መልኩ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡
ተቋማቱ ይህ መመሪያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው መመሪያው ከመጽደቁ እና ወደ ተግባር ከመቀየሩ በፊት የህዝብ አስተያየት መድረክ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡