ለሃጂ ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን መካከል የአምስት ሰዎች ህይወት አልፏል
ኢትዮጵያውያኑ ሃጃጆች ህይወታቸው ያለፈው በሙቀት ሳቢያ ሳይሆን በመኪና አደጋና በህመም ነው ብሏል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት
በዘንድሮው ሃጂ በከባድ ሙቀት ምክንያት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል
ለሃጂ ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን መካከል የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት አስታወቀ።
ምክርቤቱ ባወጣው መግለጫ በሳኡዲ በተከሰተው ከባድ ሙቀት ምክንያት በኢትዮጵያውያን ሃጃጆች ላይ ጉዳት አልደረሰም ብሏል።
“በሙቀቱ ሳቢያ የተጎዳ ባይኖርም በመኪና አደጋ አንድ አባት ሲሞቱ፣ አራት ሰዎች በህመም ሕይወታቸው አልፏል” ይላል መግለጫው።
በ1445ኛው የሀጂ ስነስርአት የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን እንደአመጣጣቸው እንደሚመለሱ ምክርቤቱ ገልጿል።
በዘንድሮው የሃጂ ስነስርአት በከባድ ሙቀት ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺህ መሻገሩ በትናንትናው እለት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተለያዩ ሀገራትን ዲፕሎማቶችን ዋቢ አድርጎ ይፋ ባደረገው አሃዝ እስከትናንት ድረስ የ10 ሀገራት ዜግነት ያላቸው 1081 ሃጃጆች ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
እስካሁን የገቡበት ያልታወቁ ሃጃጆች ፍለጋ የቀጠለ ሲሆን፥ የሟቾቹ ቀብር መጀመሩም ተጠቁሟል።
ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የውጭ እና ከ300 ሺህ በላይ የሳኡዲ ዜጎች የተሳተፉበት የዘንድሮው ሀጂ በከፍተኛ ሙቀት ተፈትኗል።
የሀገሪቱ የሜዪዮሮሎጂ ማዕከልም በዚህ ሳምንት የመካ ሙቀት 51 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴልሺየስ መድረሱን መግለጹ ይታወሳል።
በዚህም እድሜያቸው የገፋና የተለያዩ ህመሞች ያሉባቸው ከ2 ሺህ 700 በላይ ሃጃጆች ሆስፒታል ገብተው እየተካከሙ እንደሚገኙ ተገልጾ ነበር።
ሚሊየኖች በሚሳተፉበትና ከእስልምና አምስት ምሰሶዎች አንዱ በሆነው የሃጂ ስነስርአት መጠኑ ይለያይ እንጂ በየአመቱ የሃጃጆች ሞት ይመዘገባል።
ከስምንት አመት በፊትም በሚና ጠጠር ውርወራ ሲካሄድ በተፈጠረ መረጋገጥ ከ2 ሺህ በላይ ሃጃጆች ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።