በቱርክ አደራዳሪነት የተካሄደው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ስምምነት ምን ምን ይዟል?
ኢትዮጵያ ከሶማሊላድ ጋር ከአንድ ዓመት በፊት የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል
ሶማሊያ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል የአዲ አበባውን ስምምነት ውድቅ አድርጋለች
በቱርክ አደራዳሪነት የተካሄደው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ስምምነት ምን ምን ይዟል?
ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በአዲስ አበባ የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባውን ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣም ነበር፡፡
የሁለቱም ሀገራት ወዳጅ የሆነችው ቱርክ በአንካራ የውይይት መድረክ ያዘጋጀች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ በትናንትናው ዕለት ወደ አንካራ አቅንተው ነበር፡፡
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የሁለቱን ሀገራት መሪዎች በተናጠል አግኝተው እንዳወያዩ እና ልዩነቶቻቸውን በስምምነት ለመፍታት መስማማታቸውን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
የአንካራ ስምምነት የሚል ስም የተሰጠው ይህ ሰነድ ምን ምን ይዟል በግጭት ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያስ የተስማሙባቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
የቱርክ ኮሙንኬሽን ስምምነቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አደራዳሪነት የተካሄደው ስምምነት ለሁለቱም ሀገራት በሚጠቅም መንገድ መጠናቀቁን አትቷል፡፡
እንደ መግለጫው ከሆነ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ለማክበር የተስማማች ሲሆን የባህር በር ፍላጎቷንም ይህን በማይጥስ መልኩ ታካሂዳለች ተብሏል፡፡
እስከ መጭው የካቲት ወር መጨረሻ ቀናት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥም ሁለቱ ሀገራት የጋራ የቴክኒክ ቡድን በማዋቀር በአራት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የሚያስችላትን ስምምነት ለማጠናቀቅም እንደተስማሙ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ ነጻነት እና ዓለም አቀፍ ህጎችን ለማክበር መስማማታቸውም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሶማሊያ ለከፈሉት መስዋዕትነት ሶማሊያ እውቅና እንደምትሰጥም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ እንዲፈጸም ሁለቱም ሀገራት ተስማምተዋል ሲልም መግለጫው አትቷል፡፡
ይሁንና ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መበላሸት ዋነኛ ምክንያት የሆነው እና ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የተደረገው የኢትዮጵያ - ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን በመግለጫው ላይ አልተጠቀሰም፡፡
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ከሁለት ቀናት በፊት በርበራ ወደብ የኢትዮጵያ ትራንዚት ማሳለጫ ቢሮዎች ስራ እንደጀመረ መግለጿ ይታወሳል፡፡