አውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያውያን ላይ የጣለው የቪዛ ገደብ ከምን ደረሰ?
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ለማደራደር ከኬንያ የቀረበላትን ጥያቄ መቀበሏን ገልጻለች

በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ ሁለት ሺህ ኢትዮጵያውያንን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ መመለስ ሊጀመር ነው ተብሏል
አውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያውያን ላይ የጣለው የቪዛ ገደብ ከምን ደረሰ?
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳይ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ፣ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ እና ሌሎችም ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉን የተናገሩት ቃል አቀባዩ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶች መካሄዱን ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ወደ አውሮፓ ሀገራት ለመጓዝ የሺዛ ጥያቄ በሚያቀርቡ ኢትዮጵያዊያን ላይ የጣለው የቪዛ ገደብ እንዲነሳ የተጀመረው ትረት የት ደረሰ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቅም "ኢትዮጵያ በዚህ ውይይት ወቅት ብቻም ሳይሆን የቪዛ ገደቡ እንዲነሳ ጥያቄ ካቀረበች መቆየቷን፣ ወደ አዲስ አበባ በመጣው የአውሮፓ ህብረት ልዑክም ጥያቄው ተነስቶላቸዋል። የልዑክ አባላቱም ጥያቄን መቀበላቸውን እና በቀጣይ እንደሚያዩት በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከአንድ ዓመት በፊት ወደ አውሮፓ ተጉዘው የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም በሚል የቪዛ መጠየቂያ ጊዜን ከ15 ቀናት ወደ 45 ቀናት ከፍ ማድረጉ ይታወሳል።
ሌላኛው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ያነሱት ጉዳይ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ለማቀራረብ ማቀዳቸውን አስመልክቶ ያቀረቡት ጥሪ ነበር።
አምባሳደር ነቢያት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በተለያዩ የዲፕሎማሲ መድረኮች ስትጥር ቆይታለች ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያለውን ማናቸውም ልዩነቶች በውይይት ለመፍታት ወደኋላ ብላ አታውቅም፣ ለዛም ነው በተፈጠሩ የዲፕሎማሲ መድረኮች ሁሉ ስትገኝ እና አቋማን ስታንጸባርቅ የነበረው" ሲሉ በኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የቀረበውን የማቀራረብ ጥያቄ ኢትዮጵያ መቀበሏን በተዘዋዋሪ ተናግረዋል።
በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አሁንም ትረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ከታህሳስ አንድ ቀን ጀምሮም 2 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራው 200 ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ይመጣሉ ተብሏል።
ቤሩት ያለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን መመዝገብ፣ ህጋዊ የመኖሪያ እና የጉዞ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ለሊባኖስ መንግስት እንዲከፍሉ የተተመነባቸው ክፍያ እንዲቀንስ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሆነም አምባሳደር ነቢያት ተናግረዋል።