የኢትዮጵያ መንግስት በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ የጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ
መንግስት በመብት ተሟጋቾች ላይ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ የሲቪክ ምህዳሩን መጥበብ አመላካች ነው ሲል ድርጅቱ ወቅሷል
የኢትዮጵያ አጋር ድርጅቶች መንግስት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በይፋ ማውገዝ አለባቸው ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት በሶስት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ የጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ሂዩማን ራይትስ ዎች ትናንት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
የሲቪል ማህበራትን በበላይነት የሚቆጣጠረው የመንግስት አካል የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከህዳር 14 ቀን 2024 ጀምሮ የመብትና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከልን (ካርድ) ጨምሮ ለሶስት የሲቪክ ማህበራት የእግድ ደብዳቤ ሰጥቷል።
በደብዳቤው ድርጅቶቹ በፖለቲካዊ ወገንተኝነት እና “አገራዊ ጥቅምን በሚንድ” ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበር መመላከቱን ሂውማን ራይትስ ዎች ጠቅሷል ።
የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ነፃ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በሀገሪቱ ውስጥ እንዲሰሩ የቀረውን ማንኛውንም ክፍተት እየዘጉ ነው፤ የመንግስት የቅርብ ጊዜ እርምጃም ኢትዮጵያ የመንግስትን እርምጃዎች ለመተቸት እና የሰብአዊ መብትን ለማስከበር ምቹ ካልሆኑ ቦታዎች መካከል አንዷ መሆኗን ያሳያል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ስላለው የአስተዳደር፣ የህግ የበላይነት እና የመብት ጥሰቶች በግልጽ የሚተቹት ሶስቱ ድርጅቶች የታገዱት የመንግስት የሚዲያ ህግ ማሻሻያዎችን በመተቸት በይፋዊ ደብዳቤ ከተቃወሙ ከቀናት በኋላ ነው ተብሏል።
በተቃውሟቸውም ማሻሻያው የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ተቋማዊ ነፃነት ወደ ኋላ በመመለስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቁጥጥር ስር ያደርገዋል ሲሉ መተቸታቸው ተነስቷል።
ካርድ እና ሌሎች የታገዱ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅ መሰረት የሚጠበቅባቸውን አካሄዶች አልተከተሉም፣ ህጉን ባላከበሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፈዋል የሚል አስቀድሞ የጽሁፍ ማሳሰቢያ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል ።
የመንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ከቀናት በፊት የታገዱ ድርጅቶችን በተመለከተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ ገልፀው የሲቪል ማህበረሰብ ቦታ ጠባብ ነው ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል።
ድርጅቶቹን ማገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ገለልተኛ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ ሚዲያዎችን እና ሌሎች ወሳኝ ድምጾችን ለማፈን ሰፋ ያለ የመንግስት ጥረትን ያሳያል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች።
በተጨማሪም በሁከትና ግጭት ወቅት የመንግስት ባለስልጣናት ኢንተርኔት እና የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎትን በመዝጋት በጋዜጠኞች እና በመንግስት ተቺዎች ላይ ከፍተኛ እስራት ፈጽመዋል ሲል ተችቷል ።
በሰኔ ወር የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ ከ2020 ጀምሮ በመንግስት ጫና ቢያንስ 54 ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሰራተኞችን ለስደት መገደዳቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች በመግለጫው ላይ አካቷል።
በአሁኑ ጊዜ ከትጥቅ ግጨት ጋር በተያያዙ በተለያዩ ወገኖች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በርክተዋል ያለው ድርጅቱ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችን እገዳ በአስቸኳይ በማንሳት ማህበራት የሰብአዊ መብት ተግባራቸውን በነጻነት እንዲያከናውኑ መፍቀድ አለባቸው ሲል ጠይቋል ።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል (ካርድ) አመራሮች ደረሰብን ባሉት ጫና ከሀገር መሰደዳቸው መግለጹ ይታወሳል።