የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ከወደብ ስምምነቱ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ለፊት ሊወያዩ መሆኑ ተነገረ
ቱርክ በጀመረችው ድርድር 3ኛ ዙር ውይይት ላይ ለመሳተፍ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አንካራ አቅንተዋል ተብሏል
አዲስ አበባ ከራስገዟ ሶማሊላንድ ጋር በባለፈው አመት መጀመርያ የወደብ የመግባብያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ የጎረቤታሞቹ ሀገራት ግንኙነት ሻክሯል፡
በዲፕሎማሲ ውጥረት ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች በቱርክ አንካራ ተገናኝተው ሊመክሩ መሆኑ ተነገረ፡፡
አዲስ አበባ ከራስገዟ ሶማሊላንድ ጋር በባለፈው አመት መጀመርያ የወደብ የመግባብያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ የጎረቤታሞቹ ሀገራት ግንኙነት ሻክሯል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ስለ ውይይቱ እስካሁን የተሰጠ ማረጋገጫ ባይኖርም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ቱርክ የሚያቀኑ ከሆነ ሁለቱ መሪዎች ለአመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ በዛሬው እለት ለመጀመርያ ጊዜ በቱርክ አንካራ ፊት ለፊት ይገናኛሉ።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ በተዘጋጀው ሶስተኛው ዙር ድርድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ቱርክ አንካራ በማቅናት ላይ መሆናቸውን የሃገሪቱ የዜና ወኪል በትላንትናው ዕለት ዘግቧል።
የአሜሪካ ድምጽ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጋር ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው የመሪዎቹ ውይይት የሚደረገው በኢትዮጵያ ጥያቄ አቅራቢነት ነው፡፡
ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር አዲስ አበባ የተፈራረመችው የወደብ ስምምነት እያደገ ከሚገኝው የህዝብ ቁጥር አንጻር የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል እና ለደህንነት ዋስትና የራሴ ወደብ ያስፈልገኛል ከሚል የመነጨ ስለመሆኑ ትከራከራለች፡፡
ሞቃዲሾ በበኩሏ ስምምነቱ ሉአላዊነቷን መጣሱን እና ከአንድ የክልል ግዛት ጋር የተደረገ በመሆኑ የማይሰራ እና ተቀባይነት የሌለው ነው ስትል አጣጥላለች፡፡
ባለፉት አመታት ሽብርተኝነትን በመከላከል እና በሌሎች አካባቢያዊ ግንኙነቶች ጠንካራ ወዳጅነት የነበራቸው ሀገራት በአሁኑ ወቅት በመካከላቸው የሚገኝው ውጥረት ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ስጋት ሆኗል ሲል የአሜሪካ ድምጽ አስነብቧል፡፡
ከዚህ ጋር በተያየዘም በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ እንዳይ ይሳተፉ በሶማሊያ መከልከላቸውን ተከትሎ በዚህ ወር መጨረሻ ከሀገር እንዲወጡ የሞቃዲሾ መንግስት አዟል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበሩ የድርድር ሙከራዎች በሀምሌ እና ነሀሴ ወር በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል በቱርክ አደራዳሪነት የተካሄደው ሁለት ዙር ውይይት በሶማሌላንድ ጉዳይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ባለመቻሉ ለሶስተኛው ዙር ያልታወቀ የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡
በመስከረም ወር በቻይና በተካሄደው የአፍሪካ የትብብር መድረክ ላይ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ለመገናኘት የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ ስለማድረጋቸው የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ የዘገበው የአሜሪካ ድምጽ ነው።
በወቅቱ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር አዲስ አበባ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት እንድትሰርዝ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል።
የጅቡቲ እና የሞሪታኒያ ፕሬዚዳንቶች የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ከነበሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ጋር በመሆን ሁለቱን መሪዎች ለማገናኝት ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም፡፡
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሁለቱን ሀገራት ለማሸማገል ፈቃደኛ መሆናቸውን በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡