የሰላም ሚኒስትሯ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ፡፡
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ሼክ ሰይፍ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ ተወያይተዋል።
ሁለቱ ሃገራት ያላቸው የትብብር መስኮች በተለይም በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትብብር የውይይታቸው ማጠንጠኛ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል ፖሊስ የስራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።
በተያያዘም የሰላም ሚኒስትሯ ከአቡ ዳቢ ልማት ፈንድ ጄኔራል ዳይሬክተር ሞሃመድ ሰይፍ አል ሱዌይዲ ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸው ወቅትም በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶችን መደገፍ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን መለየት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።
የልማት ፈንዱ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለሚያደርጉት ድጋፍ የሰላም ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም የልማት ፈንዱ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ዘርፎች ለሚያደርገው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል።
ጄኔራል ዳይሬክተሩ በበኩላቸው ፈንዱ በታዳጊ ሃገራት በተለይም በአፍሪካ የሚያደርገውን የልማት እንቅስቃሴ የማስፋት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ፈንዱ በአፍሪካ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የመንግስታቱን ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት በሚደግፍ መልኩ ውጤት እያመጡ መሆኑን አስረድተዋል።
የሚኒስትሯ ጉብኝት በኢትዮጵያ መንግስትና በልማት ፈንዱ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት በሚቻልበት አግባብ ላይ ለመምከር የሚያስችል እድል እንደፈጠረም ገልጸዋል፡፡
የአቡ ዳቢ ልማት ፈንድ ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ ከ32.5 ሚሊየን ዶላር በላይ ለሚያወጡ 2 የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ አድርጓል።
ምንጭ፡- ኤሚሬትስ የዜና አገልግሎት