በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የጉምሩክ ታሪፍ ዝቅተኛ እንደሚሆንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ እንደሚደረጉ ተገለፀ
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዚህም የታክስ ማሻሻያ ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው መሆኑን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ገጽ ያኘነው መረጃ ያመለክታል።
እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ እንደሚደረጉም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በታክስ ማሻሻያው መሰረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉን ሚኒስቴሩ ገልጿል
በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶ ሞቢሎችን በተመለከተም 5 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን፤ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑንም የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በኢትዮጵያ ጎዳናዎች ላይ መታየት ከጀመሩ ዋል አደር ያሉ ሲሆን፤ ግሪን ቴክ አፍሪካ የተባለ ኩባያ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በኢትዮጵያ መገጣጠም ሊጀምር መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚይ ኢንጅነር ቅደም ተስፋዬ ከወራ በፊት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሁን ለይ ከ320 በላይ በኤሌትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት መቻሉን አስታውቀው ነበር።
የተሸከርካሪዎቹ ዋጋ በነዳጅ ከሚሰሩት መኪኖች ጋር ተቀራራቢና እኩል እንደሆነ ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የጉምሩክ፣ ሱርታክስታና ተጨማሪ እሴት ታክስ ባይኖር ግን ዋጋቸው ከዚህ ይቀንስ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል።