በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መገጣጠም ሊጀምር መሆኑን ግሪን ቴክ አፍሪካ ገለፀ
እስካሁን 320 በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች ሀገር ቤት ገብተዋል
ግሪን ቴክ አፍሪካ በወራት ውስጥ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን መገጣጠም እጀምራለሁ ብሏል
ግሪን ቴክ አፍሪካ፤ በሁለት ወይም ሶስት ወራት ውስጥ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም እንደሚጀምር አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚይ ኢንጅነር ቅደም ተስፋዬ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኩባንያው የአሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ባለፈም በሀገር ቤት ለማምረት ማቀዱን አስታቀዋል።
በዚህም መሰረት ድርጅቱ በሰንዳፋ እና በድሬዳዋ ከተሞች የመኪና መገጣጠም ስራን ይጀምራል ነው ያሉት።
አሁን ለይ ከ320 በላይ በኤሌትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት መቻሉን የገለጹት ኢ/ር ቅደም፤ ተሸከርካሪዎቹ 100 በ 100 በባትሪ የሚሰሩ እንደሆኑም ገልጸዋል።
የተሸከርካሪዎቹ ዋጋ በነዳጅ ከሚሰሩት መኪኖች ጋር ተቀራራቢና እኩል እንደሆነ ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የጉምሩክ፣ ሱርታክስታና ተጨማሪ እሴት ታክስ ባይኖር ግን ዋጋቸው ከዚህ ይቀንስ እንደነበር ገልጸዋል።
ተሸከርካሪዎቹን ከውጭ ሀገራት እያሰገቡ ከመሸጥ ባለፈም በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም መታቀዱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።ይህም በሶስት ወይም በሁለት ወራት ውስጥ በሰንዳፋ እና በድሬዳዋ ከተሞች እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።
የመገጣጠሙ ሂደት በዚህ ሲቀጥል፤ በአምስት አሊያም በስድስት ዓመታት ውስጥ 60 በመቶ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ነው የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው።
መኪኖቹን በሀገር ቤት ከመገጣጠም የሚያስችል የሰለጠነ የሰው ኃይል በቻይና እየሰለጠ እንደሆነ የገለጹት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ ተጠቃሚዎች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።
መኪኖቹን በቤት ውስጥ ቻርጅ ማድረግ እደሚቻልና ከ 4 እስከ 6 ሰዓታት ውስጥ ተሽከርካሪዎቹ 80 በመቶ ቻርጅ እንደሚያደርጉም ነው የተገለጸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በኤሌትሪክ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት ቻርጅ እንዲያደርጉ ለማድረግ 40 ቦታዎች ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡
አንዱ ፈጣን ቻርጀር ማድረጊያ በአንድ ጊዜ ሁለት መኪኖችን ቻርጅ ማድረግ የሚችል ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ 80 መኪኖችን ቻርጅ ማድረግ ይቻላል ተብሏል።
ግሪን ቴክ አፍሪካ፤ የአህጉሩ ሕዝብ የኢነርጂ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል በምስራቅ፣ በምእራብ እና በደቡብ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ እየሰራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል።
ኩባንያው፤ በኤሌትሪክ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ አፍሪካ ሀገራት በማስገባት ስራውን መጀመሩን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፤ ከዚህ ባለፈም ድርጅታቸው፤ በታዳሽ ሃይል እና በአዳዲስ የኢነርጂ ምንጮች ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ነው ብለዋል።