የመጀመሪያው በራሪ መኪና በቀጣዩ ዓመት ለሽያጭ ይቀርባል ተባለ
በራሪ መኪናውን አሽከርካሪዎች ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከጎዳና ላይ ተነስቶ እንዲበር ማዘዝ ይችላሉ
በራሪ መኪናው አሁን ላይ የመብረር ፈቃድ ያገኘ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት በጎዳና ላይ የመጓዝ ፈቃድ ያገኛል
የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በሰዓት 100 ማይል መብረር ለሚችለው የመጀመሪያው የምድር እና የአየር ላይ ተሽከርካሪ ፈቃድ ሰጠ፡፡
የእንግሊዙ ጋዜጣ ዴይሊ ሜይል እንደዘገበው በምድርም በአየርም ላይ መጓዝ የሚችለው በራሪ መኪና መብረር የሚችልበትን ፈቃድ አግኝቷል፡፡
የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ፈቃድ የተሰጠው ለአውሮፕላን አብራሪዎች እና ለበረራ ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆኑን ገልጿል፡፡ ነገር ግን በራሪ መኪናው ከአንድ ዓመት ወይም ከዚያ በኋላ ፣ የመንገድ ደህንነት መስፈርቶችን ማሟላቱ ሲረጋገጥ ፣ በጎዳናዎች ላይ የሚንቀሳቀስበት ሕጋዊ ፈቃድ እንደሚሰጠው አስታውቋል፡፡
በራሪ መኪናው በጎዳናዎች ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ፈቃድ ካገኘ ፣ አሽከርካሪዎች ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መኪናውን ከጎዳና ላይ ተነስቶ በአየር ላይ እስከ 10,000 ጫማ ከፍ ብሎ እንዲበር ማድረግ ይችላሉ፡፡ ከዚያም በትንንሽ አውሮፕላን ማረፊያዎች ወይም አውራ ጎዳናዎች ላይ ማሳረፍ ይቻላል ነው የተባለው፡፡
‘ተራፉጂያ ትራንዚሽን’ በመባል የሚታወቀው ይህ በራሪ መኪና በቻይና የተሰራ ሲሆን ታጣፊ ክንፍ ያለው ነው፡፡ ክንፉ አየር ላይ በሚበርበት ወቅት የሚዘረጋ ሲሆን መሬት ላይ ሲሽከረከር ደግሞ ታጥፎ ይንቀሳቀሳል፡፡
በራሪ መኪናው (አውሮፕላኑ) እ.ኤ.አ በ2015 ለሽያጭ እንደሚቀርብ ተገልጾ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ በ2018 እና በ2019 ፈቃድ አግኝቶ ለገበያ ይቀርባል ተብሎ ነበር፡፡ ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ከታቀደው ጊዜ ቢዘገይም ፣ አሁን የበረራ ፈቃድ ያገኘው ‘ተራፉጂያ ትራንዚሽን’ በ2022 በጎዳና ላይም የሚጓዝበትን ፈቃድ ሲያገኝ በብዛት ለገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
አሁን የተሰራው ‘ተራፉጂያ ትራንዚሽን’ ሁለት መቀመጫ ያለው ሲሆን በ2018 የ 400,000 ዶላር ዋጋ ተቆርጦለት ነበር፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የበራሪ መኪና ሞዴሎችን በመስራት ላይ ነው፡፡ከነዚህም መካከል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ እና ለመብረር ወደፊት መምዘግዘግ ሳያስፈልጋቸው ከቆሙበት በቀጥታ ወደ አየር ላይ የሚነሱ እና የሚያርፉ ባለ አራት ወንበር በራሪ መኪናዎች (አውሮፕላኖች) ይገኛሉ፡፡