የሕዳሴ ግድብ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች ተጠናቀው ስራ ጀምረዋል - ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
ኢትዮጵያ ከሁለተኛው ሙሊት በፊት የሚከናወን ግንባታን ለማጠናቀቅ ከግድቡ ውሃ በማስተንፈስ ላይ ናት
ሁለቱ ማስተንፈሻዎች አጠቃላይ ዓመታዊውን የዓባይ ፍሰት የማሳለፍ አቅም እንዳላቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል
የሕዳሴ ግድብ ሁለት የውሃ ማስተንፈሻዎች ተጠናቀው በስራ ላይ መሆናቸውን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ።
ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ ሁለቱ የውሃ ማስተንፈሻዎች ግንባታ መጠናቀቁን እና ሙከራ ተጠናቆ ስራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱ የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻዎች ፣ አጠቃላይ ዓመታዊውን የዓባይ ፍሰት የማሳለፍ አቅም ያላቸው መሆኑን የገለቱት ሚኒስትሩ በግድቡ ሙሌት ወቅት የዓባይ ውሃ ወደ ታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ያለውን ፍሰት እንዲጨምር የሚያስችሉ ናቸውም ብለዋል።
ይህም ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚኖረው የውሃ ፍሰት እንደማይስተጓጎል ማረጋገጫ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ አክለው የገለጹት።
ሌሎች 13 ማስተንፈሻዎችም በመገንባት ላይ መሆናቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ ፣ ይህም ለታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ከፍተኛ ውሃ እንዲለቀቅ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም እንዲሁ ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በፊት ከግድቡ ሙሃ እየለቀቀች መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ አስታውቀዋል።
የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም ከፍተኛ የዝናብ መጠን በሚኖርበት “በሐምሌ ወይም ነሃሴ ወር ላይ ይካሄዳል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህም “በሱዳን ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋን የመከላከል ጥቅም ይኖረዋል” ብለዋል።
ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል ያለው ልዩነት እንደቀጠለ ሲሆን ፣ በሀገራቱ መካከል በቀጣይነት የሚደረገውን የሦስትዮሽ ድርድር ማን ይምራው በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት ባለመደረሱ ድርድሩ አሁንም እንደተቋረጠ ነው፡፡