ኢሰመኮ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙየዘፈቀደ እስር እና ግድያዎች አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገለጸ
ኮሚሽኑ በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠይቋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሩብ አመት የሰብአዊ መብቶች ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል
በዜጎች ላይ የሚፈጸሙየዘፈቀደ እስር እና ግድያዎች አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ አለ የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብቶች ኮሚሽን።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሩብ አመት የሰብአዊ መብቶች ሪፖርትን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም ያሉት አጋጣሚዎች ላይ ምርመራ እና መረጃ ማሰባሰብ ባደረገበት ሪፖርቱ ግጭት በሚገኝባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ዘርዝሯል፡፡
በዚህም አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል እንደሚገኙበት አመላክቷል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የጋምቤላ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ በስፋት ተፈጽመውባቸዋል ከተባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በነዚህ ስፍራዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ፣ ከይዞታ ጋር የተገናኙ እንዲሁም በታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ አካላት በሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች በሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳቶች መከሰታቸውን ነው ኢሰመኮ የገለጸው፡፡
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል መንግስት ከታጣቂዎች ጋር እያደረገ ከሚገኘው ውግያ ጋር በተገናኘ ከግጭቱ ጋር ምንም አይነት ግንኑነት የሌላቸው ንጹሀን ለእስር፣ እንግልት እና ሞት እየተዳረጉ ነው ያለው ኮሚሽኑ፥ መንግስት የንጹሀንን ሰብአዊ መብት በመጠበቅ ከትኛውም አካል በበለጠ ያለበትን ሀላፊነት በበቂ ሁኔታ እየተወጣ አይደለም ሲል ወቅሷል፡፡
በአማራ ክልል፣ ማእከላዊ ጎንደር ዞን፣ አለፋ ወረዳ፣ ሻውራ ከተማ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተደረገው ከባድ ውጊያ ከ10 በላይ ሲቪል ሰዎች ከየትኛው ወገን እንደተተኮሰ ባልታወቀ ተባራሪ ጥይት ተገድለዋል ይላል ሪፖርቱ።
ግጭቱ ከቆመና ታጣቂዎች ለቀው ከወጡ በኋላ “ታጣቂዎችን ትደግፋላችሁ”፣ “መረጃ ትሰጣላችሁ” በሚል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድና መንገድ ላይ ያገኟቸውን ሰዎች እንደገደሉ ነዋሪዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም ታጣቂዎች ከመንግስት ጋር ግንኙነት አላቸው እንዲሁም መረጃ ያቀብላሉ በሚሏቸው ዜጎች ላይ እገታ እና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን እንደሚያደርሱ ኢሰመኮ በሪፖርቱ ጠቁሟል።
በአማራ ክልል በከተሞች በተለያዩ ቦታዎች በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት እንዲሁም ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች በነዋሪዎች ላይ የደህንነት ሥጋት ከመደቀናቸው ባሻገር ለጊዜው ብዛታቸው ባልታወቁ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውም ተመላክቷል፡፡
የዘፈቀደ፣ ሕገወጥ፣ ጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦትን አስመልክቶ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ባካተታቸው መረጃዎች የተለያዩ አጋጣሚዎችን የዘረዘረ ሲሆን ከነዚህ መካከል በአስቸኳይ አዋጅ ጊዜ የተፈጸሙት ይገኙበታል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የሕግ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥልጣን የሌላቸው የጸጥታ አካላት ጭምር በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ብሔርን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ በቂ ብርሃን በማያስገባ ጨለማ ቤት መያዝ፣ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸሙባቸው እና ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተዳረጉ መሆኑን ተጎጂዎች ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ጊዜ ያበቃ ቢሆንም “ሸኔ”ን እና “ፋኖ”ን ይደግፋሉ የተባሉ ሰዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ ይገኛሉ ብሏል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን።
ምንም እንኳን ለ10 ወራት የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ያበቃ ቢሆንም በተመሳሳይ በአማራ ክልል፣ በተለይም በወልዲያ፣ እንጅባራ፣ ጋይንት፣ ደብረ ማርቆስ እና ባሕር ዳር ከተሞች በሚገኙ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ወታደራዊ ካምፖችና ሌሎች ማቆያ ቦታዎች ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው እንደሚገኙም አብራርቷል።
ሪፖርቱ በማጠቃለያው በኢትዮጵያ እገታ አስከፊ ገጽታ ያለው ችግር መሆኑን፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል፣ የመዘዋወር ነጻነትና ትራንስፖርት ላይ የተጣሉ "ሕገወጥ" ያላቸው ገደቦች ዜጎችን ሁለንተናዊ ፈተና ውስጥ መጣላቸውን ጠቅሷል፡፡
ኮሚሽኑ የግጭት ተሳታፊ ወገኖች የሰዎችን የመዘዋወር ነጻነትና በመጓጓዣ ላይ የሚጥሏቸውን ተገቢ ያልሆኑ ገደቦች እንዲያነሱ፣ ተፋላሚ ወገኖች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱና በሲቪሎች ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
መንግሥት በአማራና ኦሮሚያ ጥሰቶችን የፈጸሙና ባስፈጸሙ ኃላፊዎችና ታጣቂዎች ላይ ተዓማኒ የወንጀል ምርመራና የክስ ሂደት እንዲጀምርም ኢሰመኮ ጠይቋል።