ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ በእነማን ትወከላለች?
ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ የሚወዳደሩ አትሌቶችን ለመለየት 45 አትሌቶችን ወደ ስፔን ወስዳ አወዳድራለች
የፓሪስ ኦሎምፒክ ከሀምሌ 19 ጀምሮ በፈረንሳይ መዲና ይካሄዳል
ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ በእነማን ትወከላለች?
በየአራት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደው የመላው ስፖርታዊ ውድድር ወይም ኦሊምፒክ የዘንድሮው ውድድር በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ይካሄዳል።
ውድድሩ ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ በውድድሩ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል ናት።
በአትሌቲክስ ዘርፍ ኢትዮጵያን በውድድሩ ላይ የሚወክሉ አትሌቶች ምርጫ በስፔን ኔርሀ ትናንት ምሽት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው በ10 ሺህ ሜትር ሁለቱም ጾታ፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች እንዲሁም በ800 ሜትር ወንዶች የማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል።
ኢትዮጵያ ለፓሪስ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ውድድር ለመሳተፍ የማጣሪያውን ውድድርን በትንሹ በ27 ደቂቃ ማጠናቀቅን እንደ መስፈርት አስቀምጣለች።
በዚህም መሰረት በማጣሪያው ውድድር ከተሳተፉ 16 አትሌቶች ተሳትፈው ዮሚፍ ቀጄልቻ በ26፡31.01 1ኛ በሪሁ አረጋዊ 26፡31.13 2ኛ ፣ሰለሞን ባረጋ 26፡34.93 3ኛ እንዲሁም 4ኛ ቢንያም መሀሪ 26:37:93፣ 5ኛ ገመቹ ዲዳ 26:42:65 እና ታደሰ ወርቁ 26:46:80 6ኛ ሆነው አጠናቀዋል።
30:40 ዝቅተኛ መስፈርት በተቀመጠለት የሴቶች ተመሳሳይ ውድድር ከተሳተፉ 14 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
በዚህም መሰረት የማጣሪያ ውድድሩን ፎትዬን ተስፋይ 29፡47.71 1ኛ ፣ፅጌ ገብረሰላማ 29፡49.33 2ኛ
እንዲሁም እጅጋየሁ ታዬ 29፡50.52 3ኛ እንዲሁም አይናዲስ መብራቱ በ30:09:05 4ኛ ሆና አጠናቃለች።
ሌላኛው የማጣሪያ ውድድር የተካሄደበት የ1500 ሜትር ወንዶች ውድድር ሲሆን ውድድሩ በተቀመጠለት የሚኒማ ሰዓት 3:33.50 መሰረት አብዲሳ ፈይሳ በ3:32.37 1ኛ እና ሳሙኤል ተፈራ በ3:32.81 2ኛ ሆነው ማጣሪያውን ያለፉ አትሌቶች ተብለዋል።
1:44:70 ሚኒማ በተቀመጠለት በ800 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ ከተሳተፉ ሰባት አትሌቶች ውስጥ አንድም አትሌት መስፈርቱን ሳያሟላ ቀርቷል።