ሶማሊያ የኢትዮጵያን ጦር አስወጣለሁ ማለት እና የኢትዮጵያ ምላሽ
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተሰማሩ ስራ ተቋራጮች ላይ ጫና እያደረጉ ያሉ ሀገራት እነ ማን ናቸው?

ሶማሊያ በጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና መመረጧ ለኢትዮጵያ ምን ጥቅምና ጉዳት አለው?
በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ምላሽ
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ተልዕኮ ማብቃት ጉዳይ ዙሪያ ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ አምባሳደር ነብዩ ገለጻ ከሆነ ባሳለፍነው ሳምንት የሶማሊያ አንድ ባለስልጣን በሀገሪቱ በተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ተልዕኮ በቀጣዩ ታህሳስ ወር እንደሚያበቃ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሉት ተብሎ በስፋት ተሰራጭቷል።
ይሁንና (አትሚስ) ወይም በሶማሊያ የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረግ መሆኑን ፣ የሰላም አስከባሪው ተልዕኮም እስከ ቀጣዩ ታህሳስ ድረስ የሚቆይ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
የአትሚስ ተልዕኮ ሲጀመርም በቀጣዩ ታህሳስ እንደሚያበቃ ይታወቃል ያሉት ቃል አቀባዩ ቀጣይ ሊደረግ ስለታሰበው ተልዕኮ የኢትዮጵያ ጦር አይሳተፍም በሚል የተሰራጨው መረጃም የግለሰብ እንጂ የሶማሊያ መንግሥት ይፋዊ አቋም አለመሆኑንም ተናግረዋል።
የአትሚስ ሰላም አስከባሪ ጦር ተልዕኮ ታህሳስ ላይ ሲያበቃ በቀጣይ የታሰበው አዲስ የሰላም አስከባሪ ጦር እንደ ከዚህ ቀደሙ የሀገሪቱን ውስጣዊ ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ ተመድን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚጠብቅ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አምባሳደር ነብዩ ገልጸዋል።
ሌላኛው ቃል አቀባዩ ያነሱት ሀሳብ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ያሉ የውጭ ሀገራት ተቋራጮች ስራቸውን እንዲያቆሙ ጫና የሚያደርጉ ሀገራት ጉዳይ ነበር።
አምባሳደር ነብዩ እንዳሉት ሕዳሴ ግድቡ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግንባታው እንዲቆም የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉ እንደነበር ገልጸው ተቋራጭ ድርጅቶች ስራ እንዲያቆሙ ማድረግ አንዱ ነበር ነገር ግን ግንባታው እንደቀጠለ ነው በሚል የሀገራትን ስም ሳይጠቅሱ አልፈዋል።
ሶማሊያ ከ2025 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል እንድትሆን ተመርጣለች።
ይህ የሶማሊያ መመረጥ በኢትዮጵያ ላይ ምን ጉዳት እና ጥቅም ሊያደርስ ይችላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "የሶማሊያ መመረጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ድምጿ እንዲሰማ ያደርጋል" ሲሉ ተናግረዋል።