ኢትዮጵያ በፔሩ ዓለም አቀፍ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድር
መዲና ኢሳ የገንዘቤን ሪከርድ በማሻሻል በሴቶች 5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች
አብዲሳ ፈይሳም በወንዶች 5 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል
ኢትዮጵያ በፔሩ ዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድር
የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድር ትናንት በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ፔሩ ተጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ እየተሳተፉ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ከቀናት በፊት ወደ ሊማ ልካለች፡፡
እስካሁን በሁለቱም ጾታዎች የ5 ሸህ ሜትር ፍጻሜ ውድድር የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን በሁለቱም ጾታ ሜዳሊያ ውስጥ ገብተዋል፡፡
በ5000 ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው አሸንፈዋል፡፡
አትሌት መዲና ኢሳ ውድድሩን በ14 ደቂቃ 39 ሰከንድ 71 ማይክሮ ሰከንድ በመጨረስ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
አትሌቷ ውድድሯን ያጠናቀቀችው በገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ በ28 ሰከንዶች በማሻሻል ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በተጠናቀቀው የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ሰባተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ የነበረችው መዲና ኢሳ ከኦሎምፒክ በኋላ ሪከርድን በማሻሻል በማሸነፌ ደስተኛ ነኝ ስትል ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግራለች፡፡
ገንዘቤ ዲባባ የ5 ሺህ ሜትር ከ20 ዓመት በታች ሪከርድን በፈረንጆቹ 2010 ላይ ነበር በእጇ ያስገባችው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊዎች ምን ያክል ገንዘብ ያገኛሉ?
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መቅደስ አለምሸት በ14 ደቂቃ 57 ሰከንድ 44 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የብር ሜዳልያ ስታሸንፍ ዩጋንዳዊቷ ቻሪቲ ቼሮፕ ደግሞ ሶስተኛ በመውጣት የነሀስ ሜዳሊያ አስገኝታለች፡፡
በወንዶች የ5 ሺህ ሜትር የወንዶች ፍፃሜ ውድድር አትሌት አብዲሳ ፈይሳ የብር ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል።
ኬንያዊው አንድሪው ኪፕቱ ውድድሩን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ ሌላኛው ዩጋንዳዊ ኬኔት ኪፕሮፕ አብዲሳ ፈይሳን ተከትሎ ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ኢትዮጵያ በአንድ ወርቅ እና ሁለት ብር በድምሩ በሶስት ሜዳሊያዎች በአንደኝነት እየመራች ትገኛለች፡፡