አሁን ባለው የዋጋ ግሽበት ጥሬ ገንዘብ የት መቀመጥ አለበት?
ከአል ዐይን ጋር ቆይታ ያደረጉ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች የብር የመግዛት አቅም በመዳከሙ ጥሬ ገንዘብ ትርፍና ኪሳራን ባመዛዘነ መልኩ መቀመጥ አለበት ብለዋል
መንግስት ለዋጋ ግሽበቱ መፍትሄ የሚሆን የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግም ባለሙያዎቹ ጥሪ አቅርበዋል
በኢትዮጵያ የብር የመግዛት አቅም በየጊዜው እየተዳከመ ነው።
ለዚህም አለማቀፋዊ ሁነቶችና በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
መንግስት የብርን የመግዛት አቅም (ከዶላር አንጻር) ከማዳከሙ በፊትም ሆነ በኋላ የሚታየው የዋጋ ንረት እየጨመረ እንጂ መረጋጋት ሲያሳይ አይታይም።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙም በየቀኑ እንደ ሮኬት የሚምዘገዘገውን የዋጋ ንረት መቀነስ አይደለም ባለበት እንዲረጋጋ እንኳን ማድረግ እንደተሳነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
ታዲይ ይህ ነባራዊ ሃቅ ባለበት ሁኔታ ጥሬ ገንዘብን በባንክ ማስቀመጥ አሉታዊና አዎንታዊ ጠሜታው ሚዛን ላይ ማስቀመጥ የግድ ይላል።
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው አቶ ዋስይሁን በላይ ፥"አሁን ካለው የዋጋ ግሽበትና የባንኮች የወለድ ምጣኔ አንጻር ሲታይ ገንዘብን በባንክ ማስቀመጡ ያን ያህል የሚያበረታታ አይደለም" ይላሉ፡፡ ነገር ግን ተጽዕኖው በሰዎች የገቢ ደረጃ ወይም የመግዛት አቅም እንደሚለይ ያሰምሩበታል፡፡
በርግጥ የዋጋ ግሽበት ሲጨምር ቁጠባ መቀነሱ አይቀሬ ነው የሚሉት አቶ ዋሲሁን፥ አብዛኛው በዝቅተኛና ቋሚ ገቢ የሚተዳደረው የማህበረሰብ ክፍል ከወጪው ቀንሶ የሚቆጥበው ገንዘብ እምብዛም በመሆኑ ጉዳዩ ሊያስጨንቃቸው እንደሚችል ያምናሉ።
መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ግን የጥሬ ገንዘባቸው መቀመጫ ቦታ እንደሚያሳስባቸው ይገልጻሉ።
"ለምሳሌ ቤት የሸጠ ሰው 1 ሚሊዮን ብር በባንክ ከሚያስቀምጥ በብሩ የሆነ ነገር ገዝቶ ቢያስቀምጥ፤ የዛሬ ዓመት ቢሸጠው የዋጋ ንረቱ የሚበላውን ማካካስ ይችላል፤ በ30 በመቶ የዋጋ ግሽበትን ብናስበው ይህ ብር የዛሬ ዓመት 700 ሺህ ብር ይሆናል፤ ቦንድ ቢገዛበት ደግሞ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ገደማ ይሆናል፤ ስለዚህ የዋጋ ንረቱን መቋቋም ይቻላል፤ በባንክ ይቀመጥ ከተባለ ደግሞ ወለዱ 7 በመቶ ስለሆነ 1 ሚሊዮን ብሩ 70 ሺህ ብር ያገኛል፤ ከዚህም ታክስ ይቆረጣልና 230 ሺህ ብር ኪሳራ አለው" ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ስሌት ገንዘብ ዋጋው እንዳይወርድ በባንክ ከሚቀመጥ ይልቅ እቃ ላይ ቢያርፍ አልያም ዋጋ የሚያወጡ እንደ አክሲዮን ያሉ ግብይቶችን በመፈጸም ቢንቀሳቀስ የተሻላ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።
ሌላው የምጣኔ-ሀብት ባለሞያ አቶ መቆያ ከበደም በዋጋ ግሽበት ጊዜ ጥሬ ገንዘብ በማስቀመጥና ጥሪት በመግዛት (ቋሚ ንብረት) መሀል ሰፊ ልዩነት እንደሚፈጠር ይገልጻሉ፡፡ "ጥሪት ያለው ሰው ግሽበትን ሲያመልጥ ጥሬ ገንዘብ የያዘና ገቢው ቋሚ የሆነ (ተቀጥሮ የሚሰራ) ሰው ደግሞ ኪሳራ ይገጥመዋል" ይላሉ፡፡
ከፍተኛ ለሆነው የዋግ ግሽበት መሰረቱ የመንግስት ገቢና ወጪ አለመጣጣም እንደሆነ የሚያነሱት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው፤ መንግስት የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ገንዘብ በስፋት አትሞ መርጨቱ ግሽበቱን እያባባሰው እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
ለእርሳቸው እየተስተዋለ ላለው የዋጋ ግሽበት ቀዳሚ መፍትሄ መንግስት የበጀት ጉድለቱን የሚሞላባቸውን መንገዶች በደንብ ማጤን አለበት የሚል ነው።
በዋጋ ግሽበቱ የተከሰተውን የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድ ለማስተካከል የባንክ የወለድ ምጣኔ መታየት እንዳለበትም ነው የሚያነሱት።
"የወለድ ምጣኔ በብሄራዊ ባንክ ስለሚወሰን እንጂ በገበያው ቢወሰን ራሱን በራሱ ያስተካክል ነበር፤ ስለዚህ የግብሽቱን ያህል ባይሆንም [የወለድ ምጣኔ] በተወሰነ መልኩ መስተካከል አለበት፤ ቢያንስ ሰው ብሩን ወደ ባንክ የማስቀመጥ አዝማሚያው እንዲጨምር መስተካከል አለበት፤ ምክንያቱም የዋጋ ግሽበቱና የወለድ ምጣኔው አይገናኝም" ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ከዚህ ቀደምም የባንኮች የወለድ ምጣኔ እንዲስተካከል መጠየቁ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ እየጨመረ ከመጣው የዋጋ ግሽበት አንጻር ባንኮች ዜጎች ጥሬ ገንዘባቸውን በባንክ እንዲያስቀምጡ የሚያበረታታ የወለድ ምጣኔ ማሻሻያ በስፋት ሲያደርጉ እንዳልታየ የምጣኔ ሃብት ባለሞያው መቆያ ከበደ ይናገራሉ።
የወለድ ምጣኔው ከዋጋ ግሽበቱ ጋር ተያይቶ ይስተካከል የሚለው ጉዳይ አከራካሪ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ዋስይሁን በበኩላቸው፥ የወለድ ምጣኔው ቢስተካከል እንኳ ግሽበቱ እንደማይወርድ በመጥቀስ፤ "ይህም ሌላ ራስ ምታት ነው" የሚል ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ በተለይም ግሽበቱ እየደቆሰው ለሚገኘው ዝቅተኛ ገቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል የሚፈይደው ነገር እንደሌለም በማብራራት።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ የበጀት ስርጭትና የፕሮጀክት አፈጻጸም፣ የገቢ ምንጮችን ማሳደግ እና የመሳሉትን ጉዳዮች የፊስካል ፖሊሲውን በማሻሻል የተሻለ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ያምናሉ።
ተጨማሪ የገቢ ምንጮችን መፍጠርና ወጪን መቀነስ የዋጋ ግሽበቱን ለመቋቋም በዜጎች በኩል መወሰድ ያለባቸው አማራጮች መሆናቸውንም በማንሳት፡፡
የዋጋ ግሽበቱና የባንኮች የወለድ ምጣኔ እጅግ የተራራቀ ሆኖ ከቀጠለ ህዝቡ ገንዘቡን እያወጣ እቃ በመግዛት ግሽበቱን ሊያባብስና የቁጠባ ባህልንም ወደ ኋላ ሊመልስ ስለሚችል በአንክሮ ይታይ የሚል አስተያየታቸውንም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ለአል ዐይን አማርኛ አጋርተዋል።