በሪፖርቱ ሊባኖስ በንረቱ ክፉኛ የተጎዳች ሃገር ነች ተብላለች
ኢትዮጵያ በከፋ የምግብ ዋጋ ንረት ከተመቱ የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ሆነች።
ኢትዮጵያን ያካተተው የዓለም ባንክ ዓመታዊ የምግብ ዋስትና ሪፖርት ይፋ ሆኗል። በሪፖርቱ ሊባኖስ በንረቱ ክፉኛ የተጎዳች ሃገር ነች ተብላለች።
የምግብ ዋጋ ንረቱ በሊባኖስ 332 በመቶ ደርሷል። ይህ የምግብ ዋጋ ግሽበቱ በሃገሪቱ ከተመዘገበው አጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት በ122 በመቶ ማሻቀቡን የሚያሳይ ነው እንደ ሪፖርቱ ገለጻ።
ዚምባቡዌ፣ ቬንዙዌላ፣ ቱርክ እና ኢራን ሊባኖስን ተከትለው በንረቱ ክፉኛ የተመቱ ሃገራት ናቸው በሚል በዝርዝር ተቀምጠዋል።
የምግብ ዋጋ ንረት በዚምባቡዌ 255 በመቶ፣ በቬኔዙዌላ 155 በመቶ፣ በቱርክ 94 በመቶ በኢራን ደግሞ 86 በመቶ መድረሱም ተጠቅሷል።
በከባድ የምግብ ዋጋ ንረት ተመተዋል በሚል በሪፖርቱ ከተካተቱት ቀዳሚ 10 ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያ ካሳለፍነው ወርሃ መጋቢት ወዲህ እስከ ሰኔ በነበሩት አራት ወራት ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ንረት አጋጥሟታል ተብሏል። ንረቱ 38 በመቶ ሆኖ መመዝገቡም ነው በሪፖርቱ የተጠቀሰው።
በከባድ የብድር ጫና ውስጥ የሚገኙት ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ሊዳረጉ እንደሚችሉም ተገልጿል።
የሩሲያ - ዩክሬን ጦርነት ሃገራትን በተለይም የምግብ ዋስትና ችግር የነበረባቸውን የአፍሪካ ሃገራት ለከፋ ችግር ዳርጓልም ተብሏል።
መንግስት ያጋጠመውን በዋጋ ግሽበት ምክንያት ያጋጠመውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር መቸገሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአሁን ቀደም መግለጻቸው የሚታወስ ነው።