መንግስት የብርን ምንዛሬ ሊያዳክም ነው በሚል እየተሰራጨ ያለውን መረጃ አስተባባለ
ከአምስት ዓመት በፊት አንድ የአሜሪካ ዶላር በ23 ብር ይመነዘር ነበር
የኢትዮጵያ ብር ከአምስት ዓመት በፊት ካለው የዶላር ምንዛሬ አንጻር ከእጥፍ በላይ ተዳክሟል
መንግስት የብርን ምንዛሬ ሊያዳክም ነው በሚል እየተሰራጨ ያለውን መረጃ አስተባባለ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት ከሰሞኑ መንግስት ብር ከውጪ ሀገራት መገያያ ገንዘቦች አንጻር ያለውን የምንዛሬ ተመን ሊያሻሽል እንደሆነ በስፋት እየተወራ ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና መንግስት የብርን የውጭ ሀገራት ምንዛሬ ተመን ላይ ማሻሻያ የማድረግ እቅድ የለውም፣ እየተናፈሰ ያለው መረጃም ሀሰት ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ማክሮ ኢኮኖሚያችን እንዲረጋጋ ማድረግ ዋነኛ ትኩረታችን እንጂ የብርን ምንዛሬ የማዳካም እቅድ የለንም ብለዋል፡፡
በሚኒስትር ዴኤታው የትዊትር መልዕክት ስርም ብዙዎች ስለመረጃው አመስግነው ምላሽ ሲሰጡ ብዙዎች ደግሞ መልዕክቱን ቀደም ብለው ቢያጋሩ የተሻለ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት የብርን የምንዛሬ ተመን ሊያዳክም ይችላል የሚለው መረጃ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን የውጭ ምንዛሬ ማዘግየታቸውን፣ የህገ ወጥ ዶላር ሸመታው ደርቶ መክረሙን፣ ነጋዴዎች እና ግለሰቦችም ብራቸውን ወደ ዶላር ሲቀይሩ መሰንበታቸውን በሚኒስቴር ዴዔታው የትዊተር መልዕክት ስር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በፊት ማለትም ጥቅምት 2010 ዓ.ም ላይ የውጭ ንግድን ለማበረታታት በሚል የብርን የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲዳከም ማድረጓ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ አንድ በባንኮች የአሜሪካን ዶላር በ23 ብር ይመነዘር የነበረ ሲሆን አሁን ላይ አንድ ዶላር በ53 ነጥብ 57 ብር እየተመነዘረ ነው።
በጥቁር ገበያ ላይ ደግሞ ከ100 እስከ 120 ብር ድረስ በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡