መንግስት በባንክ በሚቀመጥ ገንዘብ ላይ የወለድ ክፍያን እንዲያሻሽል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ጠየቀ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ካለባቸው ሀገራት 9ኛ ላይ ትገኛለች ተብሏል
ዳቦ 42 በመቶ፣ አትክልትና ፍራፍሬ 19 ከመቶ ለዋጋ ግሽበቱ ድርሻ እንዳላቸው አሶሴሽኑ ገልጿል
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሲየሽን ዛሬ በሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በባንክ በሚቀመጥ ገንዘብ ላይ የወለድ ክፍያን እንዲያሻሻል ጠይቋል፡፡
በኢትዮጵያ የምርት አቅርቦት ማነስ እና የፍላጎት መጨመር ኢኮኖሚውን እየተፈታተነው መሆኑን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ገልጿል
አሶሴሽኑ የጥናት እና ፖሊሲ ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ(ዶ/ር) እንዳሉት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መኖሩን ገልጸው የምርት አቅርቦት ማነስ እና የፍላጎት መጨመር ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸው ኢኮኖሚውን እየፈተነው ነው ብሏል ማህበሩ፡፡ ባለፈው 2021 ዓመት ብቻ 1ሺህ 129 ግጭቶች የተከሰቱ ሲሆን ይህም ኢንቨስትመንትን፣ የምርት አቅርቦቶችን እና ሌሎች ለኢኮኖሚው አስፈላጊ የሆኑ ስራዎችን ማስተጓጎሉን ዳይክተሩ ደግዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ግጭቶች ከዚህ ባለፈም የተቋማት አገልግሎት መበጣጠስ እና የገንዘብ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርሷልም ብለዋል ደግዬ (ዶ/ር)፡፡
ደግዬ (ዶ/ር) መንግስት የግብርና ምርታማነትን የሚያፋጥኑ አሰራሮችን፣ የገቢ ንግድ ላይ ተመጣጣኝ ታሪፍ መጣል፣ ብክንቶችን ማስወገድ፣ የሀይል አጠቃቀም ማሻሻል እና በዋጋ ግሽበቱ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ከተቀማጭ ገንዘብ የሚሰጠው ወለድና ለብድር የሚጠየቀው ገንዘብ ምጣኔን እንዲያሻሽል የጠየቁት ዳይሬክተሩ የአቅርቦት ዋጋ ማረጋጊያ ቦርድ እንዲቋቋምም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ከምግብ ፍጆታዎች መካከል ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ካሉት የግብርና ምርቶች የእህል ዋጋ 39 ከመቶ የቁም እንስሳት ተዋጽኦ 18 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
ዳቦ 42 በመቶ፣ አትክልትና ፍራፍሬ 19 ከመቶ ለዋጋ ግሽበቱ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹት ደግዬ (ዶ/ር) የዋጋ ግሽበት በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ፍሰት ሲበዛና የሚገዛው እቃና አገልግሎት ሲያንስ የሚፈጠር ክስተት ነው ብለዋል፡፡