የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ቦንዱን የመክፈል አቅም ስለሌለ ሳይሆን አበዳሪዎችን ላለማበላለጥ በሚል የተወሰደ እርምጃ ነው ብሏል
ኢትዮጵያ ብድር መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መካተቷ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በፈረንጆቹ 2014 ላይ የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ሽያጭ አቅርቦ ነበር፡፡ ይሁንና ለሽያጭ ካቀረበችው ቦንድ ውስጥ የተሸጠው አንድ ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን ይህም የመክፈያ ጊዜው ከያዝነው ታህሳስ ወር ጀምሮ መከፈል ነበረበት፡፡
ኢትዮጵያ ቦንድ ሽጭ የሰበሰበችው አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል በየወሩ 33 ሚሊዮን ዶላር እየተጠናቀቀ ካለው ታህሳስ ወር ጀምሮ መክፈል የነበረባት ቢሆንም ሀገሪቱ ክፍያ የምትጀምርበት ጊዜው ትናንት ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ብድራቸውን በሰዓቱ መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የተካተተች ሲሆን ይህም በቀጣይ ተጨማሪ ብድሮችን እንዳታገኝ ሊያደርጋት እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት ጋና እና ዛምቢያ እዳቸውን መክፈል የማይችሉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ኢትዮጵያ ሶስተኛዋ ብድር መክፈል ከማይችሉ ሀገራት ተርታ የተካተተች ሀገር ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ ኢኮኖሚዋ በኮሮና ቫይረስ እና ጦርነት ምክንያቶች መጎዳቱን ገልጻ አበዳሪ ሀገራት እና ተቋማት የእዳ መክፈያ ጊዜ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ጠይቃለች፡፡
ይህን ተከትሎም ቻይና የተወሰኑ የብድር አይነቶች ላይ ለኢትዮጵያ የብድር መክፈያ ጊዜ ማሻሻያ ማድረጓን ያስታወቀች ሲሆን በሌሎቹ ብድሮች ላይ ደግሞ ማሻሻያ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን አሳውቃለች ተብሏል፡፡
አይኤምኤፍ ብድር ለመስጠት የሚጠቀማቸው መስፈርቶች
ኤስ ኤንድ ፒ የተሰኘው የሀገራትን ደረጃ በመመደብ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም የኢትዮጵያን ደረጃ ከዚህ በፊት ከነበረው ዝቅ ያደረገ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ከአበዳሪ ተቋማት እና ሀገራት ብድር የማግኘት እድሏን እንደሚቀንሰው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቦንድ እዳ ክፍያዋን ያልከፈለችው አበዳሪዎቿን እንደማታበላልጥ ለመግለጽ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉንም የውጭ ብድር መክፈያ ጊዜ ማሻሻያ እንዲያደርጉላት መጠየቋን የተናገሩት አቶ ማሞ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ብድር መክፈል ያልጀመረችው ተመሳሳይ አቋም እና መፍትሔ እንዲሰጠው በማሰብ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጪ በድር መጠን 28 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መናገራቸው ይታወሳል፡፡