ሶማሊያ ከዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ተሰረዘላት
እያንዳንዱ ሶማሊያዊ ከሁለቱ ተቋማት የ300 ዶላር ብድር ምህረት ተደርጎላቸዋል
የብድር ስረዛው ተከትሎ ሶማሊያ በደስታ ጭፈራ ላይ ናት ተብሏል
ሶማሊያ ከዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ተሰረዘላት፡፡
ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከዚህ በፊት ከዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ለተለያዩ ስራዎቿ የተበደረቻቸው ብድሮች መክፈያ ጊዜ ደርሶባት ነበር፡፡
ሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ፣ ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት እና በድርቅ ምክንት ብድሮቿን መክፈል እንደማትችል አስታውቃም ነበር፡፡
የዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ሶማሊያ ያለባትን የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ምህረት ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ባሬ እንዳሉት የአራት ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሀገሪቱን አመታዊ እድገት ከ60 በመቶ በላይ ድርሻ ነበረው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የሑለቱ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት እዳ ስረዛ እያንዳንዱ ሶማሊያዊ 300 ዶላር እዳ እንደተሰረዘለት ያስረዳል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በቱርክ የሚፈለገው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ወንድ ልጅ ምን ወንጀል ሰርቶ ይሆን?
ሶማሊያ በከፍተኛ እዳ ጫና ምክንት ውስጥ ካሉ የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ የነበረች ስትሆን አሁን ላይ ያለባት እዳ ከዓመታዊ ምርቷ ወይም ጂዲፒ ጋር ሲነጻጸር 8 በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አሁን ሶማሊያ በቂ ገንዘብ እጇ ላይ ይኖራታል፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ትችላለች ለዜጎቿም የስራ እድል መፍጠር ትችላለች” ብለዋል፡፡
ሶማሊያ ከፈረንጆቹ 1996 ጀምሮ ዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት የተበደረችው ብድር የነበረባት ሲሆን ከ90 በመቶ በላይ የነበረባት ብድር ተነስቶላታል፡፡
የእዳ ስረዛውን ተከትሎ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ እና ሌሎች ከተሞች ደስታ እና ጭፈራ እንደደራ ተገልጿል፡፡