ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰብዓዊና ህዝቦች መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የጀመረውን ምርመራ ማቋረጡን አደነቀች
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ለዲፕሎናቶች ማብራሪያ ሰጥቷል
ባለፉት ዓመታት ተፈጽመዋል የተባሉ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ሂደት መጀመሩ ተገልጿል
የአፍሪካ የሰብዓዊ እና ህዝቦች መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የጀመረውን ምርመራ ማቋረጡን ኢትዮጵያ አደነቀች።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ባሳለፍነው ጥቅምት በደቡብ አፍሪካ በተፈረመው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ በአዲስ አበባ ላሉ ዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በኢትዮጵያ ብዙ ለውጦች መምጣቱን፣ በትግራይ ክልል የተቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ መንግሥት እና የፌደራል መንግሥት ባደረጓቸው የጋራ ጥረቶች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳግም ስራ መጀመራቸውን፣ ለተጎጂዎች ድጋፍ መደረጉን እና የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ምላሽ ለመስጠት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል።
የሽግግር ፍትህን ለመተግበር የፖሊሲ መረጣው ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ ደመቀ የፌደራል ፖሊስ እና ፍትህ ሚንስቴር በቅንጀት ምርመራ በማካሄድ ላይ እንደሆኑም አክለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መከሰቱን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራውን ጀምሮ የነበረው የአፍሪካ ሰብዓዊ እና ህዝቦች መብት ኮሚሽን ምርመራውን ማቋረጡ የሚደነቅ ነው ሲሉም አቶ ደመቀ ለዲፕሎማቶቹ ተናግረዋል ።
ኮሚሽኑ ምርመራውን ያቋረጠው ኢትዮጵያ በራሷ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር እና አጥፊዎችን በህግ ለመጠየቅ የሽግግር ፍትህ በመጀመሯ በመሆኑ እንደሆነም ተገልጿል።
የአፍሪካ ሰብዓዊ እና የህዝቦች መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የፊታችን መስከረም በጀኔቫ በሚካሄደው የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ላይ በሚያቀርቡት ሪፖርት መሰረትም የሚቀርቡ ሀሳቦች ካሉም ለታሰበው የሽግግር ፍትህ ትግበራ በግብዓትነት ሊጠቅሙ እንደሚችሉም በማብራሪያው ላይ ተጠቅሷል።
አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው በኢትዮጵያ በሌሎች አካባቢዎችም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ፍላጎት እንዳለም ተናግረዋል።
በሱዳን ያጋጠመውን የሰላም ችግር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሆኖ ኢጋድ ያስቀመጠው የግጭት መፍቻ መንገድ ትክክለኛው መፍትሔ ማግኛ መንገድ መሆኑንም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።