በመንግስት እና በህወሓት መካከል ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት ፖለቲከኞች ምን ይላሉ?
ፖለቲከኞቹ የስምምነቱን ተፈጻሚነት በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ባካሄዱት ድርድር በዘላቂነት ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል
በአፍሪካ ህብረት መሪነት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ድርድር የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በዘላቂነት ግጭት ለማቆም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ጥቅምት 24፤2013 ዓ.ም ሁለተኛ አመቱን የደፈነው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በተለይም በጦርነት ቀጠናው ባሉ ክልሎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል።
በዋናነት በአማራ እና በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች የተደረሰው የሰላም ስምምነት በጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ለሆነው ህዝብ እረፍት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የአረና ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሀፍታይ ገ/ሩፋኤል ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ጦርነቱን በሠላም ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሱን ፓርቲያቸው በፀጋ ይቀበላል ።
አረና ጦርነትን አስቀድሞ ሲቃወም ነበር የሚሉት ሀፍታይ፤ “ከጦርነት ውድመትና ልዩነት ነው የመጣው፤ የትግራይም የኢትዮጵያም ህዝብ አልተጠቀሙም” ይላሉ።
“ሀገራችን በታሪክ አይታው የማታውቀው ጦርነት ነው ያስተናገድነው። ሁለቱ ወገኖች ምንም አላገኙም። [ስምምነቱ] ቢያንስ የሕዝብን ሞትና ውድመትን ያስቀራል። ጦርነቶች በስተመጨረሻ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው የሚፈቱት።” ሲሉ የሰላም ስምምነቱን ዋጋ ተናግረዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የአማራ ህዝብ የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊና ገፈት ቀማሽ መሆኑን በማንሳት ስምምነቱን “በጥሩ ጎኑ” መመልከታቸውን ለአል ዐይን ተናግረዋል።
በስምምነቱ የህውሓት ትጥቅ መፍታት፣ ለተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመር፣ ህዝባዊ ግንኙነቶችን ለማሳደግ እንደሚሰራ መመላከቱን በተስፋ ያነሳሉ።
“የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ [የአማራ፣ ትግራይማ አፋር ህዝቦች] ከደረሰበት ደም መፋሰስ፤ ከደረሰበት ውድመት ለማገገም፣ ለሰላም እድልና ጊዜ የሰጠና ያመጣ በመሆኑ ከነችግሮቹም በበጎ የሚታይ ነው።” በማለት አዎንታዊ ጎኑን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ በድርድሩ በጦርነቱ “ቀጥተኛ” ተሳታፊና ከፍተኛ ጉዳትን ያስተናገዱ ኃይሎች በአግባቡ አልተወከሉም ብለዋል። ጦርነቱን በዘለቄታዊነት ለመፍታት የአማራ ወኪሎች አለመሳተፋቸው ስጋት እንዲሰማቸው ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለዚህም አወዛጋቢ የወሰን ጉዳዮችን በማንሳት፤ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የአረና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ሀፍታይ ገ/ሩፋኤል ለእርሳቸው የስምምነቱ ተስፋ ከስጋቱ ያዘነበለ ነው። “ያለቀው አልቋል፤ የወደመው ወድሟል። ከዚህ የባሰ፤ ከዚህ የበለጠ ውድመት ሳይደርስ ህገ-መንግስቱን በማክበር ወደ ስምምነት መምጣታቸው ጥሩ ነው።” ይላሉ።
የስምምነቱን ተፈፃሚነት በተመለከተም ልበ ሙሉ ናቸው። ለዚህም ምክንያት ሲያቀርቡ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረትን የመሰሉ ጫና ፈጣሪዎች በድርድሩ አሻራ በማሳረፋቸው ነው። ከስምምነቱ በሚያፈነግጡ አካል ላይ ጫና ስለሚደርስ፤ ስምምነቱ መሬት እንደሚረግጥ ያላቸውን እምነት ለአል ዐይን ተናግረዋል።
“[ሁለቱ ኃይሎች] ወደ ስምምነቱ የመጡት በበጎ ፈቃደኛነት ሳይሆን በዓለም ጫና ስለሆነ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ይቸግራል ብዬ አላስብም።” ብለዋል።
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ግን ቅቡልነቱና ተፈፃሚነቱ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። በዋናነት ድርድሩ እንደ አማራ ያሉ የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊዎች አለመወከላቸው ለቅቡልነቱም፣ ለተአማኒነቱም እንዲሁም ለተፈፃሚነቱ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል። በሰላም ስምምነቱ እንደ ወልቃይትና ራያ ያሉ የይዞታ ውዝግብ ያለባቸው ስፍራዎችን “በህገ-መንግስቱ መሰረት ይፈታሉ” መባሉም ሌላ ጥርጣሬ ያስነሳባቸው ጉዳይ መሆኑንም አልሸሸጉም።
ሀፍተይ ገ/ሩፋኤል ችግሮች ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ እንዲፈቱ ስምም ላይ መደረሱን ለትግበራው እንደ ምሰሶ ያደርጋሉ። ሀገሪቱ ወደ ዘላቂ ሰላም ለመጓዝም ስምምነቱን “መንገድ ጠራጊ” ብለውታል።
“ጦርነት እየተካሄደ እርቅ የሚባል ነገር የለም፤ ይቅርታ የሚባል ነገር የለም። ተኩስ ከቆመ በኋላ ሌላው ቀስ በቀስ ይመጣል። በአንዴ ስምምነት አያቆምም። ግን የመጀመሪያው እርምጃ ተሂዷል። ተኩስ ማቆምና በሁሉም አካባቢ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ቀጣዩ ደግሞ የህዝብ ለህዝብ መቀራረብ ነው።” ብለዋል።
ከዚህ በኋላ በሚደረጉ ዝርዝር አፈፃፀሞችና ስምምነቶች አካታች እንዲሆኑ የወተወቱት የቀድሞ የአብን ፕሬዝዳንት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) እሳቸው አባል የሆኑበት የአማራ ተደራዳሪ ቡድን ወንበር እንዲያገኝ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
የሻከረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች ግንኙነት ማደስም ሌላኛው የቤት ስራ ሆኗል።
ደሳለኝ (ዶ/ር) የህዝቦቹን[የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች] የረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክና መስተጋብርን በማንሳት፤ የደረሰው መቆራቆስ ቀላል ባይባልም በአጭር ጊዜ ወደ ሰላምና እርቅ እንደሚያመሩ ባለተስፋ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት የአረና ወኪሉ ሀፍተይ ገ/ሩፋኤል “የፖለቲካ ሊሂቃኑ” ከታረቀ ወደ እርቁ ወደ ህዝቡም ይወርዳል ባይ ናቸው። ይቅርታ፣ እርቅ፣ ካሳ፣ ፍትህና ንግግር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እንደሚያድስ ተናግረዋል።
በስምምነቱ የህውሓት ትጥቅ መፍታት፣ ለተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመር፣ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ያሉ ሁሉንም የፌደራል ተቋማት መቆጣጠር፣ በትግራይ የተካሄደው ምርጫ እንዲሰረዝ እና ሌሎችም ነጥቦች ተካተውበታል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን እና በህወሓት በኩል ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ 10 ገፆችና 15 አንቀፆች ባሉት የሰላም ስምምነት ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የተደረሰው ስምምነት ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል፡፡
ህወሓት የተደረሰው ስምምነት በፍጥነት ወደ ተግባር አንዲቀየር እንደሚፈልግ የተናገሩት ቃል አቀባዩ ህወሓት ስምምነቱን የፈረመው ለትግራይ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ያሰፍናል ብሎ በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በሰላም ስምምነቱ ያሰበው እንደተሳካለት ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በድርድሩ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ያነሳቸው ሁሉም ሀሳቦች ተቀባይነት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት ቁርጠኛ መሆኑን እና በትግራይ መልሶ ግንባታ እንደሚካሄድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡