ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በመንግስትና በህወሓት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ምን አሉʔ
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “ስምምነቱ ህወሓትን ለማዳን በዋሽንግነት ግፊት የተደረገ ነው” ብለዋል
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ በጦርነቱ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር አንድ አካል ሆነን ሰርተናል ብለዋል
የሰላም ስምምነቱ “ህወሓትን ለማዳን” በዋሽንግነት ግፊት የተደረገ ነው ሲሉ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በትናንትናው እለት ሀገራዊ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ባነሱበት ከኤሪ-ቲቪ ጋር በነበራቸው ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ ላይ ነው፡፡
ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለመቋጨት በቅርቡ በመንግስት እና ህወሐት የተደረሰው ስምምነት፤ ፕሬዝዳንቱ በቃለ ምልልሱ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩበት አብይ ጉዳይ ነበር፡፡
- “የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ መውጣት ለዘላቂ ሰላም ቁልፍ ሚና አለው”- አሜሪካ
- የኤርትራ ሰራዊት እንቅስቀሴ ስጋት የፈጠረባቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ምን እያሉ ነው?
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሰነድ ድንጋጌ ከሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡
ከክልሉ እንዲወጡ ከሚጠበቁት ኃይሎችም የኤርትራ ወታደሮች ዋናኛ መሆናቸውም በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ኤርትራ በጦርነቱ መሳተፏንም ሆነ የወታደሮቹ ከትግራይ መውጣትን በተመለከተ "ጸረ-ማጥቃት" ነበር በሚል ጥቅል አገላላጽ ያለፉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ በነበሩ ሶስት ዘመቻ ምእራፎች ስኬታማ እንደነበሩም በኩራት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ህወሐት በጦርነቱ " በመቶ ሺዎች " የሚቆጠሩ የትግራይ ታጣቂዎች አጥቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ “አቅማቸውን የማያውቁ” ያሏቸውን የህወሓት አመራሮች ትምህርት የወሰዱበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በሰላም ስምምነት ሽፋን ጦርነቱ መሉ በሙሉ እንዳይጠናቀቅ እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ህዳር 2022 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ስለተደረሰው ስምምነት ያላቸውን አስተያየት የሰነዘሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ስምምነቱ "በአሜሪካ የተዘየደ ታክቲክ" መሆኑ ተናግረዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ “ህወሓትን ለማዳን” በዋሽንግነት ግፊት የተደረገ ነው ያት ፕሬዝዳንቱ " እኛ ብዙ የሚያሳስብ ነገር አልነበረንም፡፡ ስምምነት ተፈርሟል? ጥሩ፤ የተፈረመው ይተግበር። ሳይተገበር ይህ ነው ያ አይደለም ብለን መናገር አንችልም፤ ሲተገበር የምናየው ይሆናል" ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ቃለ ምልልስ አሁንም ድረስ አነጋጋሪ ስለሆነው ስለ ኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መውጣት ጉዳይ ያሉት ነገር የለም፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በኬንያ ናይሮቢ ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ላይ በሰጡት መግለጫ ስለጉዳዩ ተጠይቀው “ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚመለከት ነው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውም ይታወሳል፡፡
የኤርትራ ባለስልጣናት እንደፈረንጆቹ 2020 በተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ መሳተፋቸው የተመለከተ መረጃ ውድቅ ሲያደርጉ ከቆዩ ከወራት በኋላ ማመናቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በትናንትናው ቃለ ምልልሳቸው ያረጋገጡትም ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመተባበር የህወሓት ታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሳቸውን ነው፡፡
" ከምንም በላይ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጋር አንድ አካል ሆነን ስለሰራን ትልቅ ልምድ ወስደንበታል" ሲሉም ነው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፡፡
የነበረው ሁኔታ በቀጠናው ላይ "ሰላም ለማምጣት" ትልቅ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት ነበር ሲሉም አክለዋል፡፡
ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንዲህ መሆነ ለአሜሪካና ቅጥረኞቿ የሚዋጥ አይደለም ብለዋል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፡፡
" ይህቺ ለአሜሪካ ትልቅ የራስ ምታት ናት ፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሰላም ሲኖር" የማይጠብቁት ስለሆነ አያስደስታቸውም ሲሉም ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ኤርትራ ከአሜሪካ ጋር ያት ግንኙነት ጥሩ ነው የሚባል እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ አሜሪካ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ በኤርትራ ወታደራዊ እና ደህንነት ሹሞች ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው፡፡
የአሜሪካን ክስ ውድቅ የምታደርገው ኤርትራም እንዲሁ በቀጠናውም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚስተዋሉ ቀውሶች የአሜሪካና አጋሮቿ የተሳሳተ ፖሊሲ ውጤት መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ ትደመጣለች፡፡
ኤርትራ ከማንም ጋር ተስማምታ መኖር የምትሻ ሀገር መሆኗ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ ሌላውን እየኮረኮመች የዓለም ኃያል ሆና መኖር የምትሻውን አሜሪካ አካሄድ ዓለምን ወደ ቀውስ የሚከት አደገኛ አካሄድ ነው ሲሉ ሞግተዋል፡፡
የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተመለከተም፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን በነበሩበት ወቅት የሻከረውን ግንኙነት በንግግር ለመፍታት ጥረቶች ተጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ በጆ-ባይደን አስተዳደር ዘመን ምንም ተስፋ ሰጭ ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
የኤርትራ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በነበራቸው ተሳትፎ ከባድ የሚባሉ የስብአዊ መብት ጥሰቶች እንደፈጸሙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲገልጹ ይደመጣል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ የሚቀርበው ክስ “ሆነ ተብሎ የተፈበረከ ውሸት ነው” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቃለ ምልልሳቸው ትልቅ ጊዜ ሰጥተው ባወሩበት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጉዳይ በህወሓት ታጣቂዎች እና የትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰውን ኪሳራና ጉዳት ቢናገሩም፤ በኤርትራ በኩል ስለደረሰው ኪሳራ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
በኬንያው መግለጫቸውም በጦርነቱ ምን ያህል የኤርትራ ወታደሮች እንደተገደሉ ተጠይቀው ምላሽ ሳይሰጡ ያለፉበት አጋጠሚም አይዘነጋም፡፡