የመስቀል ደመራ በዓል ተከበረ
የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል
የደመራ በዓል መስቀሉን ለማግኘት ንግስት ኢሌኒ ፍላጋ ያስጀመሩበት ሰለሆነ በአማኞች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው
የመስቀል ደመራ በዓል በዛሬው እለት በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ውሏል።
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በመስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ክርስቲያን ፓትያርክ በጽእ ወቅዱስ አብነ ማቲያስ፣ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለበዓሉ ታዳሚዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ማትያስ፤ “እግዚአብሄር ፍጥረታትን መልካም አድርጎ እንደፈጠረ ቅዱስ መጽሃፍ ይነግረናል፤ ነገር ግን ብዙ ሳይቆይ በፍጥረታት መካከል መጋጨት እና አለመግብብት ችሏል” ብለዋል።
ግጭቶች በሰው በሰው ልጆች መካከል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ፍጥረታት መካከል ሲፈጠር ተስተውሏል ያሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ፤ ይህም ሊሆን የቻለው በሳጥናኤል እና በአዳም በጥፋታቸው ሲረገሙ ነው፤ ፍጥረታትም የዚሁ እርግማን ተሸካሚ ስለሆኑ ነው።
ዛሬም ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ፍጥረታት እር በእርስ ሲጣሉ ማየት የተለመደ ሆኗል፤ ይሁን እንጂ መፍትሄ የሌለው ቸግር የለም ብለዋል ብፁዕ አቡነ ማትያስ።
በየጊዜው ለሚከሰቱ አለመግባባቶች መፍትሄው ይቅርታ እና እርቅ ነው፤ በእርቅ መንፈሳዊ ኃይል ጠብ ብዙ ጊዜ ሲሸነፍ አይተናል ሲሉም ተናረዋል።
ጠብን በእርቅ፣ በደልን በይቅርታ ከህደትን በሃይማኖት በማከም መኖር ይችላል ያሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ፤ የሰው ልጅ ካልሰነፈ በስተቀር ይህንን የማድረግ አቅም አለው ብለዋል።
እግዚአብሄርም ለበደለው የሰው ልጅ አንድ ልጁን በመስቀል ላይ ቤዛ በማድረግ ይቅርታን በማድረግ የይቅርታን ታላቅነት አሳይቷል ብለዋል።
ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር መታረቅ ማለት ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅ ነው፤ ስለዚህ ከእግዚአብሄር ለመታረቅ አጠገባችን ካሉ ወንድምና እህቶቻችን ጋር መታረቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የመስቀሉን በዓል ስናከብር ከመስቀሉ መገኘት ባሻገር ማስታወስ ያለብን መስቀሉ ከኛ የሚፈልገው ያሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ የመስቀሉ መልእክት በሰው ልጆች መካከል ፍቅር፣ አንድነት፣ እኩልነት፣ አዘኔታ እና መተሳሰብ በምእላት ተጠብቆ እንዲኖር ነው ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ማትያስ በመልእክታቸው፤ ከእልከኛ አስተሳሰብ እንውጣ እና የእግዚአብሄርን ድምጽ እንስማ፤ በተግባርም እናሳይ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
እግዚአብሄር ግጭቱን አስወግዶ፣ ሰላሙን እርቁን እና አንድነቱን እንዲያመጣልን፤ እኛም የእርቅ እና የይቅርታ ሰው ሆነን እንድነገኝ በርትተን እንጸል ብለዋል።
የደመራ በዓል መስቀሉን ለማግኘት ንግስት ኢሌኒ ፍላጋ ያስጀመሩበት ሰለሆነ በአማኞች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሀይማኖታዊ በዓል ነው።
የደመራ በዓል ከመስቀል አደባባይ ባሻገር ምእመናን በየቤተክርስቲያቱና በቤታቸው ደመራ በመለኮስ ያከብሩታል።
የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባሉት ባህላዊ ትእይንቶቹ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።