የደመራ በዓል ተከበረ
የደመራ በዓል መስቀሉን ለማግኘት ንግስት ኢሌኒ ፍላጋ ያስጀመሩበት ሰለሆነ በአማኞች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው
መስቀል ሰላምንና እርቅን ያስገኘ፤ መጨረሻ ተግባሩንም ሰውን በማዳን ያጠናቀቀ ነው- ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ
የመስቀል ደመራ በዓል በዛሬው እለት በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ውሏል።
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በመስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ክርስቲያን ፓትያርክ በጽእ ወቅዱስ አብነ ማቲያስ፣ የኢትዮጵያ ፐሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ መስቀል ከሁሉ በላይ ነው ብለዋል።
መስቀል በውስጡ ሰፊ እና ጥልቅ የሆነ ሚስጥረ መለኮት ይዟል ያሉት አቡነ ማቲያስ፤ መስቀል ሰላምን እና እርቅን ያስገኘ፤ መጨረሻ ተግባሩንም ሰውን በማዳን ያጠናቀቀ ነው ብለዋል።
መዳን ሲነሳ ከእሱ በፊት ጉዳት እንዳለ መገንዘብ አያዳግትም ያሉት አቡነ ማቲያስ፤ ከዘመነ ክርስቶስ በፊት በመስቀል ላይ የሚሰቀለው ሀጢያተኛ ብቻ ነበር ብለዋል።
ይሁን እንጂ እግዚአብሄር ሰውን ከፍዳ መርገም ሊያድን መርገም ሳይኖርበት በእርጉማን ፈንታ ቤዛ ሆኖ ሊያድንን ተግባሩን በመስቀል ላይ ፈፀመ ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህም በእግዚአብሄር እና በአዳም መካከል እርቅ ወረደ ሰላምም ሰፈነ፤ ሰውም ከፍዳ መርገም ዳነ ብለዋል። ቅዱስ መጽሃፍ ይህንን በተመለከተ “በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰ ደሙ በሰማይ እና በመድር ላሉ ሁሉ ሰላምን አደረግ ይላል” ብለዋል።
የእኛ ሰላም እና እርቅን እለት እልተ በየጊዜው ያለመቋረጥ ልንተገብረው ይገባል ሲሉም መልእክት አስተላፈዋል።
በልብሳችን ያሳተምነው፤ በአካላችን የተነቀስነው ትምህርተ መስሰቀል ለጌጥ አይደለም፤ ይልቁንም በመስቀሉ በእኛ እና በፍጥረታት መካከል ሰላምን ለመጠበቅ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
ትምህርተ መሰቀሉ ሰላምና እርቅ እስከ ውስጠ አካላችን ዘልቆ እንዲገባ ሊያስተምረን እና ሊቀሰቅሰን ይገባል ያሉ ሲሆን፤ የሰው ልጅ የሰላም እና የእረቅ አማባሳደር ሆኖ በእግዚአብሄር የተሰየመ መሆኑን ሊያውቀው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በዓለም ላይ ሰላም ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፍን ጠንክረን እንስራ ሲሉም ብጹዕ አቡና ማቲያስ ጥሪ አቅርበዋል።
የደመራ በዓል መስቀሉን ለማግኘት ንግስት ኢሌኒ ፍላጋ ያስጀመሩበት ሰለሆነ በአማኞች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሀይማኖታዊ በዓል ነው።
የደመራ በዓል ከመስቀል አደባባይ ባሻገር ምእመናን በየቤተክርስቲያቱና በቤታቸው ደመራ በመለኮስ ያከብሩታል።
የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባሉት ባህላዊ ትእይንቶቹ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።