“መጠፋፋቱ ቢበቃንና ምድሪቱን የሰላም አየር እንድትተነፍስ ብንፈቅድላት”- አቡነ ማቲያስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የገና በአልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እርቅን በማስቀደም ሰላም እንዲሰፍን ጠይቀዋል
ፓትሪያርኩ በመልዕክታቸው “አለም ከፈጣሪ ርቃ መጓዟ የምንመለከተውን የከፋ ችግር እንድትጋፈጥ አድርጓታል” ብለዋል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ለዕርቅ እና ሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠየቁ፡፡
ቅዱስነታቸው በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት መገዳደል እና መጠፋፋት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
“ጠቡ ፣ ጥላቻው፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ለወንድሜ ከማለት ይልቅ ለኔ ለኔ ማለቱ ሲጎዳን እንጂ ሲጠቅመን ኣላየንም ያሉት ፓትሪያሪኩ፤ ወደ ልባችን እንመለስና በፍቅር፣ በዕርቅና በእኩልነት፣ በስምምነትና በወንድምነት ወደሚገኝ አንድነት እንምጣ፤ የልደቱ መዝሙር ያስተማረን ይህና ይህ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሌሎቹ ክፍለ ዓለማት እንደሆነው ሁሉ በሀገራችን የተከሠተው አላስፈላጊ ግጭት ብዙዎችን አሳጥቷል፤ ብዙዎችንም ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ የሰቆቃ ኑሮ እንዲገፉ አድረጓል ብሏል መግለጫው፡፡
አቡነ ማቲያስ በመልዕክታቸው “ልጆቻችን ምናለ ከእንግዲህ ወዲህ ቢበቃንና ምድሪቱን የሰላም አየር እንድትተነፍስ ብንፈቅድላት፤ ይህ የወቅቱ የቤተክርስቲያናችን ዋነኛ መልእክትና ጥሪ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰላምን ጨምሮ መልካም ነገር ሁሉ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው “የእግዚአብሔር ክብርና ሰላም በእጅጉ የተሳሰሩና የተቆራኙ ናቸው፤ እኛ እግዚአብሔርን ካከበርነው፣ ካዳመጥነው፣ ከታዘዝነውና ከተከተልነው ሰላም አለ፤ ለሱ ካልታዘዝንና እሱን ካላከበርን ግን ዘላቂ ሰላምን ማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ መሆኑን” አመላክተዋል፡፡
ዛሬ በሁሉም የዓለማችን ማዕዘን የሚታየው የሰላም መደፍረስ እግዚአብሔርን ካለማክበር ለሱ ካለመታዘዛችን የተነሣ እንደሆነ መዘንጋት እንደሌለበትም አመላክተዋል፡፡
ክርስቲያኖች በአእምሮ ጐልብተው በሥነ-ምግባር ታንጸው ጤናማ ሕይወትን እንዲመሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓለ ልደት ወይም ገና ሲከበር “ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ፍቅርን፣ ነገረ ዕርቅንና ነገረ ሰላምን በማኅበረሰባችን የማሥረጽ አጀንዳ ይዘን ልናከብር ይገባልም” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “እግዚአብሔር በምድራችን ሰላምን ያወርድ ዘንድ ካለን ከፍለን ለተፈናቃዮች፣ ለነዳያን እና ለአካል ጉዳተኞች በመለገስ በዓሉን በመንፈሳዊ ደስታና በሰላም ይከበር ዘንድ” ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች በአማራ ክልል ከባለፈው ሁለት አመት ጀምሮ፣ በኦሮሚያ ክልል ከአመታት በፊት ጀምሮ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል
መንግስት በአማራ ክልል "ጽንፈኛ" ከሚላቸው የፋኖ ታጣቂዎችና በኦሮሚያ ክልል ደግሞ መንግስት በሽብር ከፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር በሚያካሃዳቸው ውጊያዎች በውጊያ አውድ እና ከአውድ ውጭ ንጹሃን ለሞት፣ ለመፈናቀል እና ለማህበራዊ ምስቅልቅል መዳረጋቸውን ኢሰመኮን ጨምሮ በርካታ የመብት ተቋማት ሪፖርት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስታቸው ግጭቱን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በተጋጋሚ ገልጸዋል።
ነገርግን የፌደራል መንግስት ከታጣቂ ቡድኖች ጋር በይፋ የጀመረው ንግግር የለም፣ ግጭቱም እንደቀጠለ ነው።
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ግጭቱ በውይይት እንዲፈታ በተለያየ ጊዜ ተናግረዋል።