አምባሳደሯ አቡነ ማትያስን በመኖሪያ ቤታቸው አነጋጋሩ
ፓትርያርኩ በቅርቡ ሰጡት ስለተባለው ቃለ መጠይቅ አንስተው መወያየታቸውንም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው
በንግግራቸው ስለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታዎች በተለይም ስለ ትግራይ ሰብዓዊ ድቀቶች አንስተዋል
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጌታ ፓሲ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን በመኖሪያ ቤታቸው ተቀብለው አነጋጋሩ፡፡
በንግግራቸው ስለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታዎች በተለይም ስለ ትግራይ ሰብዓዊ ድቀቶች እና በቅርቡ ሰጡት ስለተባለው ቃለ መጠይቅ አንስተው መወያየታቸውን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
አምባሳደር ጌታ ፓሲ አቡነ ማትያስ ወደፊት በኤምባሲው በሚካሄዱ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዘዋቸዋል፡፡
አቡነ ማትያስ ባሳለፍነው ወር የተናገሩት ነው በሚል ከሰሞኑ በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች የተለቀቀው የምስል ንግግር መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በ“አፈና ውስጥ” መሆናቸውን የተናገሩት ፓትርያርኩ በትግራይ ስላለው ሁኔታ ለመናገር እንዳልቻሉ ገልጸው ነበር፡፡
በክልሉ እየተካሄደ ያለው “የአረማዊነት ሥራ ነው” ብለዋል ስራው እንዲቆም ለማድረግ እና ለመቃወም ደጋግመው ሞክረው አለመሳካቱን በመጠቆም፡፡
በትግራይ ያለው ከሌሎች አካባቢዎች የተለየ እና እጅግ የከፋ በጭካኔ የተሞላ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
“የትግራይ ህዝብ ህይወቱንም ንብረቱንም መብቱንም ተገፎ ካላጠፋንህ ብለው ይኸው እስካሁን ድረስ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ”ም ነበር ፓትርያርኩ ያሉት፡፡
ሆኖም ንግግሩ “የግላቸው እንጂ ቤተክርስቲያኒቷን የሚወክል አይደለም” በሚል ቅዱስ ሲኖዶሱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
እንደ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ መግለጫ አቡነ ማትያስ ተናገሩት ተብሎ በማኀበራዊ መገናኛዎች የተሰራጨው ንግግር “ቅዱስ ሲኖዶሱ ያልተወያየበት እና ያልወሰነዉ ጉዳይ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱን የማይወክል ነዉ”፡፡
ሲኖዶሱ ጉዳዩን አስመልክቶም በቀጣይ በአጀንዳ የተያዘ እና ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚወያይበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡