አዲሱ ዓመት የሰላምና የህዝቡ አንድነት የሚጸናፀት ይሁን- ብጹዕ አቡነ ማቲያስ
“የአዲስ ዓመት የሰላምና የእድገት ምኞታችን ወደ ተጨባጭ ፍሬ ሊደርስ የሚችለው በሥራ ብቻ ነው” ብለዋል
አዲስ የዘመን ስጦታን በአዲስ አስተሳሰብና አሠራር ተቀብለን ካልተጠቀምንበት ከምኞትና ከቃላት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ለ2014 ዓ.ም የእንኳእ ደረሰችሁ መልክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ 2013 ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ 2014 ዓመተ ምሕረት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ብለዋል።
ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ አንሥቶ እስካሁን ባለበት ብቻ ቆሞ የኖረበት ዘመን የለም ያሉት አቡነ ማቲያስ፤ በየጊዜው አዳዲስ የአሠራር ስልቶች እየተፈጠሩ፣ በቀጣይም በሌላ አዲስ ስልት እየተተኩ ይኖራሉ፤ ይህም ቋሚ የሆነ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው ብለዋል።
“ከዚህ አኳያ በተሰናባቹ በ2013 ዓመተ ምሕረት ማብቂያና በአዲሱ 2014 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ቆም ብለን ልናስበው የሚገባ ነገር አለ” ሲሉም ገልጸዋል።
“ይህም በተሰናባቹ ዓመት የነበረንን አጠቃለይ ሥጋዊና መንፈሳዊ ተግባር መመርመር ሲሆን ያልሠራንባቸው አጋጣሚዎች ካሉም በአዲሱ ዘመን አካክሰን በመሥራት ያመለጠንን ሁሉ በእጥፍ ሠርቶ ለመተካት ጠንክሮ መሥራት ያስፈለጋል” ብለዋል።
“አዲሱ ዓመት ሲመጣ የደስታና የተሐድሶ ልቡና ዘመን እንዲሆንልን ከመመኘቱ ጋር በብሩህ ተስፋ መቀበላችን መልካም ነው፤ ይሁንና የሰላምና የእድገት ምኞታችን ወደ ተጨባጭ ፍሬ ሊደርስ የሚችለው በሥራ ብቻ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
“በየጊዜው አዲስ የሆነ ራዕይ፣ አዲስ የሆነ አሠራር፣ አዲስ የሆነ ጥበብ፣ አዲስ የሆነ ዘመን፣ አዲስ የሆነ ጤንነት ወዘተርፈ ከመስጠት የተቋረጠበት ጊዜ የለም” ያሉት ብጹዕ አቡነ ማቲያስ “ይሁንና እግዚአብሔር የሰጠንን አዲስ የዘመን ስጦታ በአዲስ አስተሳሰብና አሠራር ተቀብለን ካልተጠቀምንበት አዲስ ዘመን ማለቱ ብቻ ከምኞትና ከቃላት ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም” ብለዋል።
“እግዚአብሔር በዓሉን የደስታና የጤና፣ዘመኑን የምሕረትና የሰላም ያድርግልን” ያሉ ሲሆን፤ “ለሀገራችንና ለመላው ዓለም ሰላምን ይስጥልን፤ ሕዝባችንን በፍቅርና በአንድነት ያጽናልን፤ የተዘራውን ዘር፣ የተተከለውን ተክል ይባርክልን፤ የተወለዱትን ሕፃናት ያሳድግልን” ሲልም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።