በዓለ ትንሣኤውን ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ልናሳልፈው ይገባል- አቡነ ማቲያስ
የኃይማኖት አባቶች ለትንሳዔ/ፋሲካ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
የትንሳኤ በዓል የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ እንዲከበር የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አስተላልፈዋል
“በዓለ ትንሣኤውን ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ልናሳልፈው ይገባል” ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ አስተላፉ።
የኃይማኖት አባቶች በነገው እለት የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልእከታቸው፤ “በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚከበረው የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ያለው መንፈሳዊ ትርጉም እጅግ የላቀ ነው፤ እግዚአብሔር ፍጥረታትን በሙሉ በተለይም የሰው ልጅን ሲፈጥር በፍጹም ፍቅር ነው፡፡
“በዓለ ትንሣኤ የእግዚብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል” ብለዋል ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልእከታቸው።
በመሆንም “በዓሉን ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት ከኛ ጋራ በመንፈስና በሞራል በዓለ ትንሣኤውን እንዲያሳልፉ እናደርግ ዘንድ መንፈሳዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል፤ በበኩላቸው የትንሣኤ በዓል የክርስቶስን መነሣት ያስተማረን የምሥራች መሆኑን ተናግረዋል።
የትንሳኤ በዓል ሲከበር የችግሮች ሁሉ መውጫ ቁልፍ ሰላም ብቻ በመሆኑ በትንሣኤው ብርሃን ለሀገርና ለህዝብ የሰላም መሣሪያ በመሆንና ለሰላም በመፀለይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ፤ ምዕመኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በማገዝ ሊሆን ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉም በፍቅር ልብና በይቅርታ ለሰላምና አብሮነት በመጸለይ በዓሉን እንዲያከበርም መልክት አስተላልፈዋል።