ኢትዮጵያ በጋምቢያ የህጻናት ሞትን ያስከተሉ 4 የመድኃኒት ምርቶች ሁኔታን እየተከታተልኩ ነው አለች
የዓለም ጤና ድርጅት አራቱ ሽሮፖች ለከፍተኛ የኩላሊት ጉዳትና ለህጻናት ሞት ምክንያት ሳይሆኑ አይቀርም ብሏል
በጋምቢያ በ4 የህንድ ምርት ሽሮፖች ሳቢያ 66 ህጻናት ሞታቸው ተነግሯል
በጋምቢያ የህጻናት ሞትን አስከትለዋል የተባሉ 4 የመድኃኒት ምርቶች ሁኔታን እየተከታተለ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ፣ በቅርቡ በጋምቢያ ለህጻናት ሞት ክስተት በሆኑት አራት የመድኃኒት ምርቶችን የአለም ጤና ድርጅት በተሰጠው መረጃ መሰረት ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል።
ማስጠንቀቂያ የወጣባቸው አራቱም ምርቶች፣ ፐሮመየታይዚን ኦራል ሶሉሽን፣ ኮፌክሳምሊን በየቢ ካፍ ሲሩፕ፣ ማኮፍ ቤቢ ካፍ ሲሩፕ እና ማገሪፕ ኤን ኮልድ ሲሩፕ መሆናቸውን አስታውቋል።
የእነዚህ ምርቶች አምራች የሆነው በህንድ ሀገር የሚገኘው ማይድን ፋርማቲኩዋልስ መሂኑን ያድታወቀው ባለስልጣኑ፣ ድርጅቱ ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እውቅና ያልተሰጠው ፤ምርቶቹም ያልተመዘገቡ ከመሆናቸውም በላይ በየትኛውም ህጋዊ በሆነ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ ያልገቡ መሆናቸውን አስታውቋል።
ነገር ግን በተለያየ መልክ ህጋዊ ባልሆነ መልኩ ቢገባ እንኳን በሚል አስፈላጊውን የቁጥጥር እና ክትትል ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም ገልጿል።
በአፍሪካዊቷ ጋምቢያ የህንድ ምርት ከሆኑ አራት መድሃኒቶች ጋር በተያያዘ የ66 ሕጸናት ህይወት ማለፉ መገለጹ ይታወሳል።
የዓለም ጤና ድርጅት የጋምቢያው የሕጸናት ሕልፈት ከሽሮፖቹ ጋር ሳይገናኝ አይቀርም በሚል አራቱ ሽሮፖች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ዓለም አቀፍ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
ሽሮፖቹ ለከፍተኛ የኩላሊት ጉዳት እና ለ66 የሕጻናት ሞት ምክንያት ሳይሆኑ አይቀርም ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት።
ሽሮፖቹን መጠቀም በተለይ በሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ወይም ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
የህንድ ማዕከላዊ የመድኃኒት ጥራት ተቆጣጣሪ ድርጅት ሽሮፖቹ ለጋምቢያ ብቻ መላካቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት መግለጹን ኤአፍፒ የዜና ዘግቧል።
ምንም እንኳ እነዚህ አራት የሕጻናት ሽሮፕ አይነቶች የተሰራጩት በጋምቢያ ብቻ ነው ቢባልም መደበኛ ባልሆነ የገበያ ስንሰለት ወደ ተቀሩት ጎረቤት አገራትም ሳይሰራጩ አይቀርም ተብሏል።